ቀጥታ፡

የዘንድሮ የፈተና ሥርዓት በራስ የሚተማመን ትውልድ ለመፍጠር መሠረት ነው - ተፈታኞችና ፈታኝ መምህራን

ሚዛን አማን/ዲላ፣ ጥቅምት 02 ቀን 2015 (ኢዜአ) ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲ የተካሄደው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና አሰጣጥ ሥርዓት በራስ የሚተማመን ዜጋን መፍጠር የሚያስችል መሠረት የሚጥል መሆኑን  ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች እና ፈታኝ መምህራን ገለጹ።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ው ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከማዝ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የመጣው ተማሪ ደምሴ ኮምቲኬስ "መጀመሪያ በውስጣችን የነበረውን ፍርሃትና መረበሽ አስወግደን በተረጋጋ መንፈስ መፈተን ችለናል" ብሏል።

"በፈተናው ለኩረጃ ምንም አይነት ሃሳብ ሳይኖረን የራሳችንን ብቻ ባነበብነው መጠን በሰላም ሰርተን ወጥተናል " ብሏል ።

የፈተናው አሰጣጥ ስርአት በቀጣይ ተማሪዎች በራስ የመተማመን ባህልን ለማዳበር ከወዲሁ ጠንክረው እንዲማሩ የሚያስችል መሆኑን ጠቁሟል።

ከጂማ ዩኒቨርስቲ ወደ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ሄደው ተማሪዎችን የፈተኑት መምህር ምናለ ፍቃደ በበኩላቸው የፈተናው ሂደት ሰላማዊ እንደነበር ተናግረዋል።

ተማሪዎች የሚሰጣቸውን መመሪያ አክብረው መፈተናቸውን ገልጸው የፈተናው ስርአት ማንም ተማሪ በራስ የግል ብቃት ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት እንዲችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ስርአቱ ተጠናክሮ ከቀጠለ ተማሪዎች በኩረጃ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡበትን ያልተባ አካሄድ በማስቀረት  ሊከተል የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ለመቀልበስ እንደሚያስችል አመልክተዋል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ በሚዛን፣ አማን፣ እና ቴፒ ካምፓሶቹ የመጀመሪያ ዙር የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ የሆኑ 16 ሺህ ተማሪዎችን በሰላማዊ ሁኔታ ማስፈተኑን የዩኒቨርስቲው መማር ማስተማር ምክትል ፕሬዚዳንት እጩ ዶክተር ካሳሁን ሙላት ተናግረዋል።

"የፀጥታው ኃይል ከዩኒቨርስቲው አስተዳደር ጋር ያደረገው የተቀናጀ የአሰራር ሥርዓት ሂደቱን ስኬታማ አድርጓል" ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ "የፈተና ስርአቱ ብቁ ዜጋን ለማፍራት የሚያስችል አንድ የለውጥ ምዕራፍ ነው" ሲሉም አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በሁለተኛው ዙር ለሚገቡ የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች ቀድሞ ከተደረገው ተጨማሪ ዝግጅት በማድረግ በተመሳሳይ መልኩ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንደሚያስፈትን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል የዲላና ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲዎች የመጀመሪያው ዙር የማህበራዊ ሳይንስ  የ12 ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም