ቀጥታ፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የአፍሪካ ሰብዓዊና የህዝቦች መብቶች ፍርድ ቤት በትብብር ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ

ጥቅምት 2/2015 /ኢዜአ/ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአፍሪካ ሰብዓዊና የህዝቦች መብቶች ፍርድ ቤት በትብብር ለመስራት ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ  መዓዛ አሸናፊ  እና የአፍሪካ ሰብዓዊና የህዝቦች  መብቶች  ፍርድ ቤት  ፕሬዝዳንት ኢማኒ ዳውድ  ባውድ ፈርመዋል።

በስምምነቱ  መሰረት ሁለቱ ፍርድ ቤቶች ልምድ ልውውጥን ጨምሮ በተለያዩ  ጉዳዮች ላይ በትብብር  ይሰራሉ።

የፌደራል ጠቅላይ  ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ  መዓዛ አሸናፊ በዚሁ  ጊዜ እንዳሉት፤ ስምምነቱ በተለይም በአቅም  ግንባታ ስራዎች ላይ በጋራ  ለመስራት  ዕድል የሚፈጥር  ነው።

ስምምነቱ የጥናትና ምርምር፣ የስልጠና እና አውደ ጥናቶችን በጋራ ለማካሄድ የሚያስችል እንደሆነም አብራርተዋል።

የአፍሪካ ሰብዓዊና የህዝቦች  መብቶች  ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ኢማኒ ዳውድ ባውድ በበኩላቸው፤  ስምምነቱ የኢትዮጵያ  መንግስት ሰብዓዊ  መብቶች ጥበቃ ላይ ቁርጠኛ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ በሀገር ደረጃ ስምምነት ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያው  መሆኑን ጠቁመው  ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም