ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ሳሕለ ወርቅ የበጀት ዓመቱን ዋና ዋና የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ሲገልጹ ያቀረቡት የሰላም አማራጭ ሃሳብ ይደገፋል - ኢሕአፓ

ጥቅምት 02 ቀን 2015 (ኢዜአ) ፕሬዝዳንት ሳሕለ ወርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የበጀት ዓመቱን ዋና ዋና የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ሲያስቀምጡ በሰላም አማራጭነት ያቀረቡትን ሃሳብ የሚደግፈው መሆኑን ኢሕአፓ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፤ ኢትዮጵያ በአሸባሪው ሕወሃትና መሰል አሸባሪ ቡድኖች እየተፈተነች መሆኑን ይናገራሉ።

አሸባሪ ቡድኖች የባዕዳን ተልዕኮ በማንገብ የአገርን ሕልውና እየተፈታተኑ ባሉበት ወቅት በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጉዳዩ የአገር ጉዳይ በመሆኑ ካለምንም ልዩነት ከመንግስት ጎን መቆማቸውን ተናግረዋል።

ከተመሰረተ ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረው ኢሕአፓ ከሕወሃት ጋር ከስምንት ጊዜ በላይ በድርድር ሂደት ክህደት እንደተፈጸመበት አስታውሰው፤ አሸባሪው ሕወሃት ለሰላም ሂደት የሚታመን እንዳልሆነ አንስተዋል።

ያም ሆኖ መንግስት ለሰላማዊ አማራጭ ያሳየው ተደጋጋሚ ጥረት አድንቀው፤ ፕሬዝዳንቷ በህዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ያደረጉት ንግግር ይህንን ያረጋግጣል ብለዋል።

ለሰላም አማራጭ መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራና በተለይም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ላይ መንግስት የማይናወጥ አቋም እንዳለው መግለፃቸውን አስታውሰዋል።

በመሆኑም ፕሬዝዳንቷ ያደረጉት ንግግር የበጀት ዓመቱን ዋና ዋና የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ሲያስቀምጡ በሰላም አማራጭነት ያቀረቡትን ሃሳብ ኢሕአፓ የሚደገፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ጉዳይ መላ ኢትዮጵያዊያን በጋራ መቆም አለባቸው ሲሉም ምክትል ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ችግሮች በምክክር ለመፍታት አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ስራ መጀመሩና ፕሬዝዳንቷ በጉዳዩ ላይ የሰጡት ትኩረትም ተገቢ ነው ብለዋል።

ኢሕአፓ በኢትዮጵያ ምክክር ተድርጎ አገራዊ ቅራኔዎች እንዲፈቱ ሲወተውት መቆየቱን አስታውሰው፤ አሳታፊ፣ ገለልተኛና አካታች ምክክር ለልዩነቶች መፍትሔ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም