የኢትዮጵያውያን ኃብት ለሆኑ የማህበረሰብ ዕውቀቶች ጥበቃ እየተደረገ አይደለም ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያውያን ኃብት ለሆኑ የማህበረሰብ ዕውቀቶች ጥበቃ እየተደረገ አይደለም ተባለ
አዲስ አበባ መስከረም 12/2011 በኢትዮጵያ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፉ የመጡ የማህበረሰብ ዕውቀቶች ጥበቃ እየተደረገላቸው አለመሆኑን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የተደራጀ የመረጃ ስርዓትና የህግ ማዕቀፍ አለመኖር ጥበቃ እንዳይደረግ ማነቆ ሆኗል ተብሏል። ባህላዊ አልባሳት፣ መድሃኒቶች፣ ጭፈራዎችና ዘፈኖች በኢትዮጵያ ጥበቃ ሊደረግላቸው ከሚገቡት የማህበረሰብ ዕውቀቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። እንዲህ ዓይነቶቹ ማህበረሰባዊ የእውቀት ምንጮች በዓለም አቀፍ ደረጃ “ኢንደስትሪያል ዲዛይን'' በሚል ዘርፍ ተለይተው ጥበቃ ይደረግላቸዋል። እውቀቶቹ በቅርጽ፣ አይነትና ዲዛይን ተመዝግበው በአለም አቀፍ ደረጃ ጥበቃ እንዲደረግላቸው በተደራጀ የመረጃ ቋት መቀመጥ ይኖርባቸዋል። ሆኖም በኢትዮጵያ የአገር ባህል አልባሳትን ጨምሮ ባህላዊ መድሃኒቶችና ሌሎችም የማህበረሰብ ዕውቀቶች በዚህ መልኩ ተመዝግበው የባለቤትነት ጥበቃ እየተደረገላቸው አይደለም። በጽህፈት ቤቱ የአህምሯዊ ንብረት ጥበቃና ቴክኖሎጂ ሽግግር ድጋፍና ማማከር ቡድን መሪ አቶ ስንታየው ታደሰ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ የተደራጀ የመረጃ ስርዓትና የህግ ማዕቀፍ አለመኖር ጥበቃ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እያደናቀፈው ነው። በዚህም የተነሳ ከአገር በቀል እውቀቶች መገኘት ያለበት ጥቅም እየባከነ ነው። የተደራጀ የመረጃ አያያዝ ስርዓት አለመዘርጋት እንዲሁም የህግ ማዕቀፍ አለመኖር ጥበቃውን ለማድረግ ፈተና መሆኑንም ይናገራሉ። "ለማህበረሰብ ዕውቀቶች በቂ ጥበቃ ለማድረግ ቤተ መጽሃፍት ማቋቋምና የተደረጀ የመረጃ ቋት ማዘጋጀት ያስፈልጋል" ያሉት አቶ ስንታየው ጽህፈት ቤቱ ከአለም አእምሯዊ ንብረት ተቋም ጋር በመሆን የህግ ማዕቀፍ የማዘጋጀት ስራዎችን መጀመሩን ተናግረዋል። በተለይም በቅርቡ የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳት ዲዛይን ተመሳስሎ እየተዘጋጀ ከቻይና እየገባ በአገር ውስጥ የሽመና ባለሙያዎችና ነጋዴዎች ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ኢዜአ ባለሙያዎቹን አነጋግሮ ከሰሞኑ ዘገባ መስራቱ ይታወሳል። የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆኑ እሴቶችንና የማህበረሰብ ዕውቀቶችን በመረጃ አደራጅቶ በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍና በሌሎች አገሮች ቅጂ እንዳይደረጉ መጠበቅ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፊነት እንደሆነ የእደ ጥበብ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።