የኢንዱስትሪ ግብኣት አቅርቦት እጥረት ለማምረቻ ኢንዱስትሪው እድገት እንቅፋት ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዱስትሪ ግብኣት አቅርቦት እጥረት ለማምረቻ ኢንዱስትሪው እድገት እንቅፋት ሆኗል
አዲስ አበባ መስከረም 12/2011 በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የኢንዱስትሪ ግብኣት አቅርቦትና ጥራት እጥረት የማምረቻ ኢንዱስትሪው በሚፈለገው መጠን እንዳያድግ ዋነኛ ማነቆ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ገለፀ። ድርጅቱ ተወዳዳሪነቱን በማጎልበት 'ውጤታማ ያደርገኛል' ያለውን የሰባት ዓመት ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን አስታውቋል። የድርጅቱ ሰራተኞች ባለፈው ዓመት አፈፃፀምና በቀጣይ እቅድ እንዲሁም በድርጅቱ ስትራቴጂ ላይ ዛሬ ባካሄዱት ስብሰባ መክረዋል። በዚሁ ወቅት እንደተገለፀው፤ የአገሪቱ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፉ ዋነኛ ችግር የኢንዱስትሪ ግብዓቶች በተፈለገው ጥራት፣ መጠንና ጊዜ አለመገኘት ነው። መንግስት ይህንን ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅትን ከአራት ዓመታት በፊት ማቋቋሙ ይታወቃል፡፡ ሆኖም አስተማማኝ የግብዓት አቅርቦትን በመዘርጋት የማምረቻውን ዘርፍ በሚፈለገው መጠን መደገፍ እንደተሳነው የድርጅቱ የሰው ኃብት ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳሙኤል መላኩ ተናግረዋል። ድርጅቱ የማምረቻው ዘርፍ የሚጠይቀውን የግብዓት አቅርቦት በማሟላት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የመተካትና የውጭ ምንዛሬ ወጪን የመቀነስ ኃላፊነትም ተጥሎበት ነበር። ባለፉት አመታት ድርጅቱ አመታዊ እቅዶችን ብቻ በማውጣትና የአሰራር ስርዓቶችን በመፍጠር ሲንቀሳቀስ ቢቆይም ውጤታማ መሆን ባለመቻሉ የግብዓት አቅርቦት ላይ የተገኘው ውጤት አጥጋቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም ነባሩን አሰራር ለመቀየር የሚያስችለውን አቅምና አዲስ አሰራር ለመገንባት የረዥም ጊዜ ስትራቴጂ መንደፍ ማስፈለጉን አቶ ሳሙኤል አመልክተዋል። የሁለተኛ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን የትኩረት አቅጣጫዎችንና ዓለም ዓቀፋዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት እንደዚሁም የደንበኞችንና ባለድርሻ አካላትን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ስትራቴጂው ከተያዘው በጀት አመት ጀምሮ እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ የሚደረግ ነው ተብሏል። ስትራቴጂው የተቀረፀው በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመዘየድ የሚያስችል ጥናትን መሰረት በማድረገ ነው። ስትራቴጂው ድርጅቱ ለአገሪቱ የዘርፉ እድገት ከሚጠበቅበት ኃላፊነት ባሻገር በአፍሪካ ደረጃ በግብዓት አቅርቦት የጎላ ሚና እንዲኖረው የሚያስችለውን ቁመና መቀዳጀትን ጭምር ታስቦ የተቀረፀ ነው ተብሏል። የድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንዳለህ ሀብታሙ በበኩላቸው በ2010 በጀት አመት በማምረቻው ዘርፍ ከፍተኛ የግብዓት አቅርቦት እጥረት እንደነበር ጠቅሰው በተያዘው በጀት አመት የግብዓት አቅርቦት እቅዱን ካለፈው በጀት አመት በአምስት እጥፍ ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸዋል።