ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት በርካታ ምቹ ሁኔታዎች ያሏትና ቀዳሚ መዳረሻ አገር መሆኗን የሶፍሌት ኢትዮጵያ ብቅል ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተናገሩ

ጥቅምት 2/2015/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንት በርካታ ምቹ ሁኔታዎች ያሏትና ቀዳሚ መዳረሻ አገር መሆኗን የሶፍሌት ኢትዮጵያ ብቅል ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዣን ቤንኖይት ቪቬት ተናገሩ።

በብቅል ማምረትና ሌሎች የግብርና መስኮች በተለያዩ ሀገራት የተሰማራው የፈረንሳይ ኩባንያ የሆነው ሶፍሌት በአፍሪካ የመጀመሪያ የኢንቨስትመንት መዳረሻውን ኢትዮጵያ ላይ አድርጓል።

በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ60 ሚሊዮን ዩሮ ያስገነባውን የብቅል ፋብሪካም በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት አስመርቋል።

ኢትዮጵያ ሰፊ የግብርና እንቅስቃሴ ያለባትና በገብስ ምርት ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗ የብቅል ፋብሪካዎችን ለመሳብ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል።

የሶፍሌት ኢትዮጵያ ብቅል ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዣን ቤንኖይት ቪቬት ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የብቅል ፋብሪካውን ለመክፈት ያለውን ምቹ ሁኔታ ዳሰሳ አድርገው ነበር።

በዚህም ከሰፊ የግብርና እንቅስቃሴው ባሻገር ከሶፍሌት ጋር የሚሰሩ ዓለም አቀፍ የቢራ ፋብሪካዎች በኢትዮጵያም ሥራ መጀመራቸው ፋብሪካውን ለማቋቋም ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለኢንቨስትመንት  ጠንካራ የአመራር ውሳኔ እየሰጠ መሆኑን ፋብሪካውን በማቋቋም ሂደትና ከተቋቋመ በኋላም መመልከታቸውን አንስተዋል።

የተቋማት የተቀናጀ ድጋፍ፣ የአሌክትሪክና መሰል አገልግሎቶች በበቂ  ሁኔታ እየቀረበ በመሆኑ ሶፍሌት ኢትዮጵያ የብቅል ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ እንዲያመርት አቅም ፈጥሮለታል ነው ያሉት።

ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለውም ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንት በርካታ ምቹ ሁኔታዎች እንዳላት ጠቅሰዋል።

በተለይም ታታሪ አርሶ አደሮችና በርካታ ወጣት የሰው ኃይል ያለባት መሆኗ ለማንኛውም የኢንቨስትመንት መስክ ምቹ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

በተለይም በግብርና ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ የአውሮፓም ሆነ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ለመጠቀም ቢመጡ አትራፊ ይሆናሉ ነው ያሉት።

ለዚህም ሶፍሌት ኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋዩን ፈሰስ ካደረገ በኋላ በየጊዜው እያስመዘገበ ያለው ስኬት ለሌሎች ኩባንያዎች መልካም ተሞክሮ እንደሚሆን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ያለውን የገበያ ሁኔታ መጥተው እንዲያጠኑም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም