ቀጥታ፡

የቱርክ ብረት አስመጭዎች ብረትና ብረት ነክ ዕቃዎችን ለኢትዮጵያ ሊያቀርቡ ነው

ጥቅምት 2/2015 /ኢዜአ/ የቱርክ ብረት አስመጭዎች ብረትና ብረት ነክ ዕቃዎችን ለኢትዮጵያ ለማቅረብ መስማማታቸውን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ፡፡

አቅርቦቱ የሚከናወነው አሊጋስ፣ ኢዝሚርና እስክንድሪያ ከተሰኙ የቱርክ ወደቦች በመነሳት ብረትና ብረት ነክ ዕቃዎችን ከሚያቀርቡ ብረት አስመጭዎችና ወኪላቸው አርካስ ጋር የተደረሰ ስምምነት መሆኑ ታውቋል።   

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ፤ ለአቅራቢዎች ቀልጣፋ አገልግሎትና በቅናሽ ዋጋ በጅቡቲ ወደብ መዳረሻዎች ለማጓጓዝ ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቂ የብረት ምርት ማቅረብ እስከምትችል ድረስ በቱርክ ሀገር ብረት ከሚያቀርቡ አስመጭዎች ፍላጎታችንን ያማከለ አቅርቦት እንዲኖር በማጓጓዝ ረገድ ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም ለቱርክ ብረት አቅራቢዎች የማጓጓዣ ቅናሽና የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል ነው ያሉት።

የብረትና ብረት ነክ ዕቃዎች የጭነት አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር የገለጹት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ሳቢያ ተቀዛቅዞ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ልታሳካው ባሰበችው ግብ ላይ የበኩላችንን ለመወጣት የማጓጓዝ አገልግሎቱን በተመጣጣኝ ዋና በሙሉ አቅም መስጠት የሚያስችል ቁመና ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ቱርክ ወደቦች የራሷን መጫኛ መርከቦች በማሰማራት የአገልግሎት ተደራሽነቱን ለማሳደግ እየሰራች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በመደበኛነት ወደ ቱርክ መጫኛ ወደቦች የራሱን መርከቦች እና ተጨማሪ ቻርተር መርከቦችን አሠማርቶ የአገልግሎት ተደራሽነቱን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑም ገልፀዋል::

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በ2014 በጀት ዓመት 51 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ ከፍተኛ ገቢ ማስመዝገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም