የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩንቨርሲቲ መሰጠቱ በተመቸና በተረጋጋ ሁኔታ ፈተናውን እንድንሰራ አስችሎናል - አካል ጉዳተኞች - ኢዜአ አማርኛ
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩንቨርሲቲ መሰጠቱ በተመቸና በተረጋጋ ሁኔታ ፈተናውን እንድንሰራ አስችሎናል - አካል ጉዳተኞች
ጥቅምት 2/2015 /ኢዜአ/ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩንቨርሲቲ መሰጠቱ በተመቸና በተረጋጋ ሁኔታ ፈተናውን እንድንሰራ አስችሎናል ሲሉ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እየተፈተኑ ያሉ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ገለጹ።
በዘንድሮ ዓመት ለአካል ጉዳት ተፈታኝ ተማሪዎች የተደረገው ድጋፍ፣ ክትትልና ምቹ ሁኔታ ለቀጣይ ጥሩ ተመክሮ ስለሚሆን ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሳይበግሯት በእግሯ እንደ እጅ በመፃፍ ፈተናውን እየወሰደች ያለችውን ተማሪ ጨምሮ ሌሎች አካል ጉዳተኞችን አነጋግሯል።
አስተያየት ሰጪዎቹ የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ በተረጋጋና በተመቸ ሁኔታ እንድንፈተን አግዞናል ብለዋል።
በተለይ ለአካል ጉዳተኞች በቂ የሆነ የመፈተኛ መሳሪያዎችን በማዘጋጀትና ድጋፍ የሚያደርጉ ሠራተኞችን በመመደብ ያለ ችግር እየተፈተንን ቆይቷል ሲሉ ተናግረዋል።
ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ ከስርቆትና ኩረጃ የፀዳ እንዲሆን፣ ተማሪዎች በሰሩት ልክ የመመዘን እድል እንዲያገኙ እንዲሁም ለትምህርት ጥራት ጠቀሜታው ከፍ ያለ
መሆኑን ገልጸዋል።
አካል ጉዳተኞች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱም ይሁን ለፈተና ሲቀመጡ ከመኖሪያ ሰፈራቸው ርቀው ስለሚሆን ለትራንስፖርት እንግልት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰው፤ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እያደሩ ፈተናውን መውሰዳቸው ከብዙ ችግር የገላገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጀመረው የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና ከ560 ሺህ በላይ ተማሪዎች በ130 ማዕከላት በተረጋጋና በሰላም ፈተናውን እየወሰዱ የሚገኙ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የሚጠናቀቅ ይሆናል።
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ እና ከኦሮሚያ የተመደቡ 12 ሺህ 56 ተማሪዎች በመፈተን ላይ ይገኛሉ።