ቀጥታ፡

በውጭ የሚኖሩ ወገኖች በአገራዊ የምክክር ሂደቱ የሚሳተፉባቸው እድሎች እየተመቻቹ ነው

ጥቅምት 2/2015(ኢዜአ)  ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገራዊ የምክክር ሂደቱ የሚሳተፉባቸው ዕድሎች እየተመቻቹ መሆኑን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ክንውኑና ቀጣይ ተግባራቱ ዙሪያ ከአፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ ከብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር ውይይት አድርጓል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ በአገራዊ ምክክር ሂደት የትኩረት ቦታዎች ፌዴራል፣ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳድሮች እና ዳያስፖራዎች በሚል በአራት ዘርፎች የተለዩ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለያዩ ክፍላተ አህጉራት ለኢትዮጵያ ጉዳይ ብዙ የሚጥሩ፣ የአገራቸውን ልማት የሚደግፉ፣እገዛና ድጋፍ የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም እነዚህን ወገኖች በአገራዊ የምክክር ሂደቱ በተለያዩ መንገዶች አንዲሳተፉ ማድረግ አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ለዚህም ኮሚሽኑ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በአጀንዳ ቀረጻም ሆነ በሌሎች የኮሚሽኑ ተግባራት የሚሳተፉበት ዕድል እየተመቻቸ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ ሂደት የዳያስፖራውን ብዛትና ተሳትፎ ግምት ውስጥ ያስገባ የልየታ ስራ በመስራት እንጂ አጀንዳ ቀርጾ እንዲያመጣ በዘፈቀደ የሚተው አለመሆኑንም አስረድተዋል።

በእስከሁኑ የኮሚሽኑ ስራዎች በርካታ ኢትዮጵያዊያና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ኮሚሽኑን ለማገዝ ቁርጠኝነታቸውን ማሳየታቸውንም ጠቅሰዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ፤ ዳያስፖራው በአዎንታም ሆነ በአሉታዊ መልኩ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም እንዳለው ጠቅሰው በምክክር ሂደቱ ተሳትፎ፣ ድጋፍና እገዛ የሚያደርጉበት ሁኔታ በመመቻቸት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም