የኢትዮጵያ ሰላም ለአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ የአገሪቷን የሰላም ጥረት ጀርመን ትደግፋለች- አምባሳደር ስቴፈን አዎር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰላም ለአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ የአገሪቷን የሰላም ጥረት ጀርመን ትደግፋለች- አምባሳደር ስቴፈን አዎር
ጥቅምት 2/2015/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ሰላም ለአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ የአገሪቷን የሰላም ጥረት ጀርመን የምትደግፍ መሆኑን በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አዎር ገለጹ።
በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ለሚከናወነው የሰላም ጥረት ጀርመን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን የአገሪቷ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት በሰላማዊ ውይይት እንዲፈታ ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀው በሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የመንግሥት የሰላም ጥረት የሚቀጥል መሆኑን ማረጋገጣቸው የሚደገፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የፕሬዝዳንቷ ንግግር በየትኛውም አጋጣሚ መንግሥት ለሰላም ዝግጁ መሆኑን የሚያረጋግጥ እንደሆነ አምባሳደሩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የጦርነት አዙሪት አብቅቶ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ጀርመን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም ለቀጣናው ብሎም ለአህጉሩ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና መረጋጋት ወሳኝ በመሆኑ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የሚከናወነው የሰላም ጥረት ውጤት እንደሚያመጣ እናምናለን ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ጀርመን የረዥም ዘመን ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት አምባሳደር ስቴፈን አዎር፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የልማትና የፖለቲካ መሪነቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
በዓለም አገሮች በተለያዩ አጋጣሚዎች ችግሮች ያጋጥማሉ፤ የኢትዮጵያም በዚሁ ማዕቀፍ የሚታይና በሰላማዊ ውይይት መፍታት የሚችል መሆኑን ጠቅሰው፤ አገሪቷን ያጋጠሟት ወቅታዊ ችግሮች ተቀርፈው የተጀመሩ የልማት እቅዶችም ለስኬት እንደሚበቁ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የጀርመን መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተጀመሩ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ለመደገፍ በጀርመን በኩል ዝግጁነት መኖሩን ተናግረዋል።