ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ደማቅ የታሪክ ምዕራፍ የአፍሪካን ሁሉን አቀፍ ወንድማማችነት በማጠናከር እናስቀጥለዋለን- ወጣቶች

ጥቅምት 2 ቀን 2015 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ደማቅ የታሪክ ምዕራፍ የአፍሪካን ሁሉን አቀፍ ወንድማማችነት በማጠናከር እናስቀጥለዋለን ሲሉ የአረንጓዴ አሻራቸውን ለማኖር ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ወንድማማችነትን የማጽናትና የማጠናከር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በአፍሪካ ለማካሄድ ወጣቶቿን ትናንት ሸኝታለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አክሊሉ ታደሰ፤ የመጪው ዘመን ጠንካራዋ አፍሪካ በወጣቶቿ ጠንካራ ህብረት እውን እንዲሆን ኢትዮጵያ የማስተባበር ሚና ይዛ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ክብርና ሉዓላዊነት በደምና አጥንታቸው አፅንተው ከማቆየት ባሻገር አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ የነበራቸውን ሚና ታሪክ በደማቁ የጻፈው ነው ሲል ተናግሯል።

በመሆኑም የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም የመጪው ዘመን ጠንካራና የበለጸገች አህጉርን እውን ለማድረግ የአፍሪካ ወንድማማችነትን የመትከል ተልዕኮ ይዘው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ደማቅ የታሪክ ምዕራፍ የአፍሪካን ሁሉን አቀፍ ወንድማማችነት በማጠናከር እናስቀጥለዋለን ሲል አረጋግጧል።

አባቶቻችን ያወረሱንን የአፍሪካ መሪነትና ጀግንነት አሁንም አፍሪካን በጋራ በማልማትና ጫናዎችን በጋራ በመመከት እንደግመዋለን ሲሉ የአፍሪካ ወንድማማችነትን የመትከል መርሃ ግብር ተሳታፊ ወጣቶች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ውስጣዊ አንድነታቸውን በማጠናከር የሰላምና የልማት ኃይል መሆናቸውን በተግባር ከማሳየት ባለፈ የአፍሪካውያን ወጣቶች አርዓያ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በጎረቤት ሀገራት የምናካሂደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም አፍሪካዊ ወንድማማችነትን በጽኑ መሰረት ላይ የምንተክልበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነትና በጋራ የመቆም ዋልታ ናት ያሉት ወጣቶቹ አፍሪካን አንድ የማድረግ እሳቤ በዚህ ዘመን በማጽናት በወጣቶቿ የጋራ ክንድ የበለጸገችዋን አፍሪካ እውን ያደርጋሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያን የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ወደተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የማስፋት ስራ እናከናውናለን ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በምታካሂደው አፍሪካዊ ወንድማማችነትን የመትከል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ100 ያላነሱ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም