ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት የሰው ሃብት ልማት ወሳኝ ነው- የምጣኔ ሃብት ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት የሰው ሃብት ልማት ወሳኝ ነው- የምጣኔ ሃብት ምሁራን
ጥቅምት 2 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገው ጥረት የሰው ሃብት ልማት ወሳኝ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር አቅም ያላቸው አልሚ ባለሃብቶችን ለመሳብ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የልማትና እድገትን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ብክነትን መቀነስና የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት ማጠናቀቅም ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚሁ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃብት ምሁራን በፕሬዝዳንቷ የቀረቡት የኢኮኖሚ እቅዶች ተገቢና ውጤት የሚገኝባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ዶክተር ቆስጠንጢንዮስ በርኸተስፋ፤ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፖሊሲና ስትራቴጂ ለዘርፉ እድገት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ተናግረዋል።
የአሥር ዓመቱ የልማት እቅድና አገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጭምር ለኢንቨስትመንት ማስፋፋት የላቀ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በቀጣይ በተለይም የሰው ኃብት ልማት በሰፊው ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ለቢዝነስ ምቹ ለማድረግ የሕዝብ አስተዳደርና የልማት አስተዳደሩን በሚገባ መቃኘት ተገቢ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የልማትና ምጣኔ ሃብት ባለሙያው ደረጄ ደጀኔ፤ የተለያዩ አገራት ማበረታቻዎችን በመስጠት ኢንቨስተሮችን የሚስቡበት አንደኛው መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።
ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ከባቢ መፍጠርና መሰረተ-ልማትን በሟሟላት የመንግሥት ዓይነተኛ ሚና መሆኑን ገልጸው፤ የሰው ሃብት ልማትም ለዘርፉ እድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለይም ከመሰረተ-ልማት ጋር ይነሱ የነበሩ ችግሮችን መቅረፋቸውን አስታውሰው፤ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የመንግሥት የፖሊሲ ክለሳና ማሻሻያ በቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
የሀብት ብክነትን ለመቀነስ በተለይም የልማትና እድገት ፀር የሆነውን ሙስና መከላከል ወሳኝ መሆኑንም ምሁራኑ አመላክተዋል።
ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና የገንዘብ መጠን ማጠናቀቅ የሀብት ብክነትን ለመቀነስ እንደሚረዳም ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት የተሰሩ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ለፕሮጀክት አስተዳደር ውጤታማነት ጥሩ ተምሳሌት ሆነው ሊወሰዱ ይገባል ነው ያሉት።