በአገራዊ የምክክር ሂደቱ የሁሉም ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
በአገራዊ የምክክር ሂደቱ የሁሉም ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ጥሪ አቀረቡ
ጥቅምት 2 ቀን 2015 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አገራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት አላማና ግቡ እንዲሳካ የሁሉም ተሳትፎና ድጋፍ እንዲጠናከር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በእስካሁን ክንውኑ እና ቀጣይ ተግባራቱ ዙሪያ ከአፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ ከብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር ትናንት ማምሻውን ተወያይቷል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በቅድመ ዝግጅትና በዝግጅት ምዕራፎች ስለተከናወኑ ተግባራት፣የቀጣይ የምክክር ሂደትና ትግበራ ዕቅዶች እና ተቋማዊ አሰራርና አደረጃጀትን አስረድተዋል።
በምክክር ሂደቱ ስለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችና ከአጋር አካላት ስለሚያስፈልጉ ትብብሮችም በዝርዝር አቅርበዋል።
የኮሚሽኑን ራዕይና ተልዕኮ የሚገልጽ አዲስ የመለያ ዓርማ ተዘጋጅቶ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን የማቋቋምና ተጫማሪ ሰራተኞችን የመቅጠር ስራዎች እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በገንዘብ ድጋፍ፣በትኩረት ቦታዎችና በአጀንዳ አቀራረብ ሂደትና ተግዳሮቶችንም በዝርዝር አንስተዋል።
በአጠቃላይ ኮሚሽነሮቹና ኮሚሽኑ በገለልተኝነትና በአሳታፊነት የተጣለባቸውን ኅላፊነት እንደሚፈጽሙ እስካሁን ጉዞው ተልዕኮውን ለመፈጸም እንደሚችል አመላካች እንደሆነ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት በመሆኑ ተልዕኮውን በተሰጠው ጊዜ እንዲፈጽም ግፊት በመኖሩ ለሚያከናውናቸው ስራዎች መንግስት ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው ብልጽግና እንደ ገዥ ፓርቲ መረዳት፣ መደገፍ፣ መሳተፍና መተግበር በሚሉ አራት ትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከኮሚሽኑ ጋር ይሰራል ብለዋል።
በምክክር ሂደቱ እንደ ባለድርሻ አካል በንቃት ከመሳተፍ ባሻገር ምክክሩ በፍጹም ገለልተኝነት እንዲፈጸም ምቹ ሁኔታዎች እንዲሚፈጠሩና አደናቃፊ አካላትንም ስርዓት እንደሚያስይዝ አረጋግጠዋል።
በሂደቱም በፍጥነትና ጥራት፣በአካታችነትና አሳታፊነት፣በኮሚሽኑና በአጋር አካላት ሚና፣በአሳታፊነት በብቃት እና በሀገር በቀልና በውጭ አካላት መካከል ሚዛኑን መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የክልል ርዕሳ መስተዳደሮች የኢትዮጵያ ችግርች በዘላቂነት የሚፈቱት በምክክር በመሆኑ የምክክር ኮሚሽኑን መደገፍ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑን በተመለከተ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ የሚስተዋሉ የግንዛቤ ክፍተቶችን ለማረምም በግንዛቤ ፈጠራ ላይ በቂ የተግባቦት ስራዎች እንደሚያስፈልጉ በመድረኩ ላይ ተነስቷል።
አገራዊ ምክክሩ በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ የጋራ መግባባት በመፍጠር አገርን በጽኑ መሰረት ላይ ማቆምና ቀጣይ መጻዒ ዕድል የሚያግዙ አጀንዳዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አንስተዋል።
በሂደቱ በልሂቃን ሳይጠለፍ ሁሉንም ህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ፣ አገር በቀል ባህልና እሴቶችን በጠበቀ፣በቦታና በአጀንዳዎች መካከል የምክክር ምህዳርን መመጠን እንደሚያስፈልግም ተወስቷል።
በዚህም የምክክር ኮሚሽኑ በየክልሎች ለሚያደርጋቸው ስራዎች ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸትና የምክክር ሂደቱን የሚያደናቅፉ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ በሰላምና ጸጥታ ዋስትና ለመስጠት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የምክክር ሂደቱም አካታች፣አሳታፊና ግልጽ በሆነ አግባብ እንዲከወንና ኮሚሽኑ በተያዘለት ጊዜ ገድብ ተልዕኮውን እንዲፈፅም በሎጀስቲክስና በሌሎች ድጋፎች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ የኢትዮጵያን ያደሩ ፈተናዎችን ለመፍታት አገራዊ ምክክር ወሳኝ መፍትሄ መሆኑ ባለድርሻ አካላት ዘንድ መግባባት እንዳለ ተናግረዋል።
በመሆኑም የምክክር ኮሚሽኑ አገራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት አላማና ግቡ እንዲሳካ የሁሉም ተሳትፎና ድጋፍ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
መንግስት ለምክክር ኮሚሽኑ ዐቢይ ትኩረት መስጠቱን ሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ያቀረቡትን የስራ አቅጣጫ እንደ አብነት አንስተዋል።
በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስራዎች ላይ የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር በጥንቃቄ መመራት እንዳለበትም ገልጸዋል።
የሀገርን ሉዓላዊነትና የህዝብን ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚገባ ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን አጀንዳ በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ በተግባር ማሳየት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ሁሉም ባለድርሻ አካል ሚናውን በአግባቡ ከተወጣ የምክክር ኮሚሽኑ በህዝብ የተጣለበትን ዓላማ እንደሚያሳካ እምነታቸውን ገልጸዋል።
መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባው የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስራውን ከጀመረ ሰባት ወራት ገዳማ አስቆጥሯል።