የአደጋ ተጋላጭነት ስጋትን ለመቀነስ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ባለሙያዎችና ሕብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል- ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
የአደጋ ተጋላጭነት ስጋትን ለመቀነስ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ባለሙያዎችና ሕብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል- ኮሚሽኑ
ጥቅምት 2/2015 ዓ.ም /ኢዜአ / በኢትዮጵያ የአደጋ ተጋላጭነት ስጋትን ለመቀነስ ፖሊሲ አውጪዎች፣ አስፈጻሚዎች፣ ባለሙያዎችና አጠቃላይ ሕብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ጉባዔ "የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መረጃ ለዘርፈ-ብዙ ምላሽ" በሚል መሪ ሃሳብ የፊታችን ዓርብ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወረርሽኞች፣ ግጭትና ሌሎች ችግሮች ዜጎችን እየፈተኑ ነው፡፡
በሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና አፋር ክልሎች የተከሰተው ድርቅ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ አሸባሪው ህወሓት የሚፈጥረው ግጭት የዜጎችን ህልውና በማናጋት ቀያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተከባም የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ በአደጋ ስጋት ቅነሳ መርሃ-ግብር ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት የበርካታ ዜጎችን ህይወት ታድጋለች ብለዋል፡፡
በ2014 በጀት ዓመት ብቻ የውሀ ማቆሪያ ገንዳ /ቢርካ/ በማዘጋጀት፣ ሕብረተሰቡን በመስኖ ልማት በማሳተፍና አፈሩ በጎርፍ እንዳይሸረሸር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በማከናወን ከ146 ሺህ በላይ ሰዎችን ከአደጋ ተጋላጭነት ስጋት እንዲወጡ ተደርጓል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ መሰረታቸውን ሳይለቁ በአደጋ ስጋት ቅነሳ መርሃ-ግብር መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ ከአመራሩ ጀምሮ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ባለሙያዎችና ሕብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡
የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ የሚያስችል የቅድመ የአደጋ ስጋት ተጋላጭነት እንዳለ የገለጹት ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ፤ በመረጃው መሰረት ሁሉም በቂ ግንዛቤ ኖሮት ወደ ሥራ መግባትና ዜጎችን ከጉዳት ማዳን ይገባል ብለዋል፡፡
በሶማሌ ክልል የአደጋ ቅነሳና መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ከፍተኛ ባለሙያ ሄኖክ በየነ፤ የሶማሌ ክልል በተደጋጋሚ ድርቅ የሚጠቃ በመሆኑ የአደጋ ስጋት ቅነሳ መርሃ-ግብር በትኩረት የሚሰራበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሕብረተሰቡ ችግሩን በሚገባ ስለሚያውቀው የአደጋ ስጋት ቅነሳ ሥራዎችን እንዲያከናውን ሲሰጡት በፍጥነት የመቀበልና የመተግበር ልምዱ እያደረገ መጥቷልም ብለዋል፡፡
በመሆኑም የሕብረተሰቡን አቅም የበለጠ በመጠቀም በክልሉ የሚከሰተውን አስከፊ የመፈናቀል አደጋ ማስቀረት የሚያስችል የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሶማሌ ክልል የአራርሶ ወረዳ ከፊል አርብቶ አደሮች ከመንግሥት የሚደረግላቸውን ድጋፍ በመጠቀም ምድረ በዳ የነበረውን አካባቢ ለልማት ማዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
በደራሽ ጎርፍና በዝናብ እየታጠበ ይሄድ የነበረው ለም መሬት ክትር በመሥራት አፈሩ እንዳይሸረሸርና ለልማት እንዲውል በማድረግ በምግብ ፍጆታ ራሳቸውን መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
በሶማሌ ክልል የጎዴ ወረዳ ከፊል አርሶ አደሮችም የዋቢ ሸበሌን ወንዝ ጠልፎ ወደ ማሳቸው በመውሰድ ለልማት እንዲውል ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡