በአገር ሉዓላዊነት፣ አንድነትና የሰላም ግንባታ ጉዳይ ያለምንም ልዩነት በጋራ የምንሰራባቸው ናቸው- የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች - ኢዜአ አማርኛ
በአገር ሉዓላዊነት፣ አንድነትና የሰላም ግንባታ ጉዳይ ያለምንም ልዩነት በጋራ የምንሰራባቸው ናቸው- የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች
ጥቅምት 2/2015 /ኢዜአ/ በአገር ሉዓላዊነት፣ አንድነትና የሰላም ግንባታ ጉዳይ ያለምንም ልዩነት በጋራ የምንሰራባቸው ናቸው ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ስድስተኛ ዙር ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን በፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በይፋ ተከፍቶ ሥራውን ጀምሯል።
ፕሬዝዳንቷ የ2015 ዓ.ም የመንግሥት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን በማመላከት ለተፈጻሚነቱ የሁሉም የጋራ ጥረት እንዲታከልበት መናገራቸው ይታወሳል።
የምክር ቤት አባላትም በአስፈጻሚ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ የተጠያቂነት አሰራር የማስፈን ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በተለይም የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ፣ የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና ሌሎችንም መሰረታዊ ጉዳዮች በ2015 ዓ.ም ትኩረት የምንሰጣቸው ይሆናል ብለዋል።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በምክር ቤቱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችም ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ በብቃት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የሁሉም የመኖር ህልውና አገር ሲኖር በመሆኑ በሉዓላዊነት፣ የአገር አንድነትና የሰላም ግንባታ ሂደት ያለምንም ልዩነት በጋራ የምንሰራባቸው ጉዳዮች ናቸው ሲሉ አረጋግጠዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ተጠሪ ዶክተር አብርሃም በርታ፤ በምክር ቤቱ የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን የአገር ሉዓላዊነትና አንድነትን በሚያስቀጥሉ አጀንዳዎችና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በጋራ መሥራታቸውን ጠቅሰዋል።
በዘንድሮው የምክር ቤቱ የሥራ ዘመንም በተለይም በአገር አንድነትና ሉዓላዊነት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ግንባታ እንዲሁም መልካም አስተዳደር ዙሪያ ያለምንም ልዩነት የምንሰራባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።
የጌዲኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትን ወክለው የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አሌሳ መንገሻ በበኩላቸው፤ በምክር ቤቱ የሥራ ዘመን የአገር አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ከመንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር ለመሥራት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር፤ በምክር ቤት መቀመጫ ባያገኙም በብሔራዊ አንድነትና የአገር ሉዓላዊነት የጋራ ጉዳያችን በመሆኑ በትብብር የምንሰራበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አስፈጻሚ አካላትን ለመቆጣጠርና ለመከታተል በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ በሚኖረን ተሳትፎ ሚናችንን በብቃት ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ የፓርቲዎቹ ተወካዮች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የጌዲኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የምክር ቤት መቀመጫ ያገኙ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች መሆናቸው ይታወቃል።