የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲፈጽም ምቹ ሁኔታዎችን እንፈጥራለን - የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች - ኢዜአ አማርኛ
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲፈጽም ምቹ ሁኔታዎችን እንፈጥራለን - የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች
ጥቅምት 1/2015 (ኢዜአ) የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲፈጽም ለኮሚሽኑ ስራዎች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ተናገሩ።
መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባው የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስራውን ከጀመረ ሰባት ወራት ገዳማ አስቆጥሯል።
በነዚህ ጊዜያት ስላከናወናቸው ስራዎችና ቀጣይ ዕቅዶቹ ዙሪያ ከአፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎን፣ ከብልጽግና ፓርቲ የፌዴራልና የክልል ጽህፈት ቤት አመራሮችና ከክልል ርዕሳን መስተዳደርች ጋር ተወያይቷል።
ኮሚሽኑ የተቋቋመለትን ራዕይና ተልዕኮ ገላጭ በሆነ መልኩ ያዘጋጀውን የመለያ ዓርማ በመድረኩ ላይ ይፋ አድርጓል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በቅድመ ዝግጅትና በዝግጅት ምዕራፎች ስላከናወናችው ስራዎች፣ የቀጣይ የምክክር ሂደት ዕቅድና ትግበራ ቅዶችና የተቋሙን አሰራርና ተቋማዊ አደረጃጀት በዝርዝር አቅርበዋል።
እንዲሁም በምክክር ሂደቱ ስለሚያጋጥሙ ስጋትና እና ከአጋር አካላት ስለሚያስፈልጉ ትብብሮች በዝርዝር አቅርበዋል።
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎችም በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የእስካሁን ስራዎችና ቀጣይ ሂደቶች ላይ ያላቸውን አስተያየትና ጥያቄዎችን አቅርበው ውይይት ተደርጓል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮችንም ተሳታፊዎች ላነሷቸው አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው ብልጽግና ፓርቲ እንደ ገዥ ፓርቲ መረዳት፣ መደገፍ፣ መሳተፍና መተግበር በሚሉ አራት ትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከኮሚሽኑ ጋር እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።
ብልጽግና በምክክር ሂደቱ እንደ ባለድርሻ አካል በንቃት ከመሳተፍ ባሻገር ምክክሩ በፍጹም ገለልተኝነት እንዲፈጸም ምቹ ሁኔታዎች እንዲሚፈጠር አረጋግጠዋል።
ኮሚሽኑ ፍጥነትና ጥራት፣ አካታችነትና አሳታፊነት፣ በኮሚሽኑ እና በባለድርሻ አካላት ሚና፣ በከፍተኛ የመፈጸም ብቃት እንዲሁም በሀገር በቀልና የውጭ አካላት ድጋፍ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲሰራም ጠይቀዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የክልል ርዕሳ መስተዳደሮች የኢትዮጵያ ችግርች በዘላቂነት የሚፈቱት በምክክር በመሆኑ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንን መደገፍ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህም የምክክር ኮሚሽኑ በየክልሎች ለሚያደርጋቸው ስራዎች ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸትና የምክክር ሂደቱን የሚያደናቅፉ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ ዋስትና ለመስጠት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የምክክር ሂደቱም አካታች፣ አሳታፊና ግልጽ በሆነ አግባብ እንዲከወንና ኮሚሽኑ በተያዘለት ጊዜ ገድብ ተልዕኮውን እንዲፈፅም የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ያደሩ ፈተናዎችን በመፍታት በመሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር ውይይት መፍትሄ እንደሆነ በባለድርሻ አካላት ዘንድ የጋራ መግባባት እንዳለ ገልጸዋል።
መንግስት ለምክክር ኮሚሽኑ ዐቢይ ትኩረት መስጠቱን ትናንት በተካሄደው የሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ያቀረቡትን የስራ አቅጣጫ እንደ አብነት አንስተዋል።
በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስራዎች ላይ የውጭ አካላት ጣልቃገብነት እንዳይኖር በጥንቃቄ መመራት እንዳለበት ገልጸዋል።
የሀገርን ሉዓላዊነትና የህዝብን ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚገባ ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን አጀንዳ በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ማሳየት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሁሉም ባለድርሻ አካል ሚናውን በአግባቡ ከተወጣ የምክክር ኮሚሽኑ በህዝብ የተጣለበትን ዓላማ እንደሚያሳካ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በተመለከተ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ የሚስተዋሉ የግንዛቤ ክፍተቶችን ለማረምም በግንዛቤ ፈጠራ ላይ በቂ የተግባቦት ስራዎች እንደሚያስፈልጉ በመድረኩ ላይ ተነስቷል።