ለአረጋዊያን የምንሰጠው ክብርና ክብካቤ ዓመቱን ሙሉ የሚዘልቅ የሁላችንም አደራና ሃላፊነት ሊሆን ይገባል-ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
ለአረጋዊያን የምንሰጠው ክብርና ክብካቤ ዓመቱን ሙሉ የሚዘልቅ የሁላችንም አደራና ሃላፊነት ሊሆን ይገባል-ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
ጥቅምት 1/2015 (ኢዜአ) ለአረጋዊያን የምንሰጠው ክብርና ክብካቤ ዓመቱን ሙሉ የሚዘልቅ የሁላችንም አደራና ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
በዓለም ለ32ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ31ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፋ የአረጋዊያን ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
እለቱን መሰረት በማድረግ የአረጋዊያን የረዥም ጊዜ ጥያቄ የነበረው የሁለገብ ማዕከል የግንባታ ዲዛይን ይፋ ተደርጓል፡፡
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፤ የአረጋዊያን ጉዳይ የሁላችንም አደራና ሃላፊነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ለአረጋዊያን የምንሰጠው ክብርና ክብካቤ የአንድ ቀን ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ የሚዘልቅ የሁላችንም አደራና ሃላፊነት ነው ብለዋል።
የአረጋዊያን ማዕከል ግንባታ እስኪጠናቀቅ ሕብረተሰቡ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
አረጋዊያንን በተመለከተ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች እንዲቀየሩ በጋራ መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ የአረጋዊያኑን የሁለገብ ማዕከል ግንባታ ለፍሬ ለማብቃት ሁሉም ሕብረተሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ማዕከሉን እውን ለማድረግ በርካታ ጥረት መደረጉንና በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦታ በማቅረብና አንድ ግለሰብ ደግሞ የግንባታ ዲዛይኑን በነፃ በመሥራት ማበርከቱን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አረጋዊያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ጌታቸው ክፍሉ፤ መንግሥት አረጋዊያን ያሉባቸውን ችግሮች በመረዳት እያደረገ ላለው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።
የአረጋዊያን ችግሮች ዘርፈ-ብዙ መሆናቸውን በመጥቀስ ለአብነት የጤና መድህን እንዲረጋገጥላቸው፣ የትራንስፖርት አቅርቦት በነፃ እንዲፈቀድላቸውና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።
አረጋዊያኑ ላነሷቸው ጥያቄዎች የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በእለቱ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባስጀመሩት የእግር ማጠብ ዝግጅት የበጎፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ የበዓሉ ታዳሚዎች ለአረጋዊያን ያላቸውን ክብር ለማሳየት እግር የማጠብ ሥነ-ሥርዓት አከናውኗል።
ከበዓሉ ጎን ለጎን በአረጋዊያን ድጋፍ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች እንቅስቃሴያቸውን የተመለከቱ አውደ-ርዕዮችን አቅርበዋል።