ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚካሄደውን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚካሄደውን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚካሄደውን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እያካሄደ ነው።
ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው ምክክር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ምሁራንና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
በክልሉ የሚካሄደውን ህዝበ ውሳኔ አፈፃፀም በተመለከተ ኦፕሬሽናል ዕቅድ ምክክር እየተደረገበት ይገኛል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት የህዝብን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በ6 ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ህዝበ ውሳኔ እንዲሰጥ ይሁንታ የተሰጠ መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝበ ውሳኔው ህግና አሰራርን ተከትሎ እንዲከናወን የሚጠበቅበተን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ የህዝብን ሃሳብ በመለካት በተሻለ የአፈፃጸም ደረጃ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
የህዝበ ውሳኔው በጋሞ፣ ጌዲኦ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ እና ወላይታ ዞኖች እንዲሁም በአሌ፣ አማሮ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ተፈፃሚ እንደሚሆን ተመላክቷል።
የህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ ታህሳስ 06/2015 ዓ.ም ለመጀመር በመነሻ ዕቅዱ የቀረበ ሲሆን ከጥር 01/2015 ዓ.ም እስከ ጥር 22/2015 ዓ.ም ደግሞ ድምጽ የሚሰጥበትና ውጤት ይፋ የሚደረግበት ጊዜ እንደሚሆን ተመላክቷል።