ቀጥታ፡

የኦዴፓ ውሳኔዎች እንደሚደግፉ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ

ጎባ/አምቦ/ ጅማ /መቱ  /ነገሌ/ፍቼ መስከረም 12/2011 የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በዘጠነኛው ጉባኤው ያሳለፋቸው  ውሳኔዎች በመደገፍ ለተግባራዊነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ እነዚህ የባሌ ጎባ ፣ አምቦ፣ ጅማ፣ መቱ ፣ ነገሌ፣ ፍቼ ከተሞችና ሊበን አካባቢ ነዋሪዎች እንዳሉት የድርጅቱ ውሳኔዎች የኦሮሞ ህዝብ ትግል ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን ያሳየ ነው፡፡ በስፍራዎቹ የሚገኙት የኢዜአ ሪፖርተሮች ያነጋገሯቸው ነዋሪዎቹ ኦዴፓ  ስያሜውን ፣ ዓርማውንና አመራሩን ጭምር በአዲስ መልክ ለመተካት ያሳየው ቁርጠኝነት ለበለጠ ትግል መዘጋጀቱን አመላካች መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከባሌ ጎባ ከተማ ነዋሪዎች መካከል  መምህር ኡመር ከድር እንደተናገሩተ ፓርቲው ያስተላለፈው ውሳኔ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ወደ ላቀ የትግል ምዕራፍ መሸጋገሩን ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ "ፓርቲው ከስያሜው ጀምሮ የወሰዳቸው ዋና ዋና ውሳኔዎች ጊዜው የሚጠይቀውን ትግልና አስተሳሰብን በመከተል በሀገሪቱ የተጀመሩ ሁለንተናዊ ለውጦችን ለማስቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል " ያለው  ደግሞ በጎባ ከተማ በንግድ ስራ የተሰማራው ወጣት ዲያ ጀማል ነው ። ፓርቲው 80 በመቶው  የአመራር ቦታ ለወጣቶች መስጠቱ የትግሉን ቀጣይነት ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅሶ ለተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጠቀሜታው የላቀ ያደርገዋል የሚል እምነት እንዳለው ወጣት ዲያ ተናግሯል ። በሌላ በኩል የአምቦ ከተማ ነዋሪ አቶ ግዛቸው መገርሣ በሰጡት አስተያየት የቀድሞው ኦህዴድ  ስያሜውን በኦዴፓ መለወጡ ትክክለኛና ወቅታዊ ከመሆኑም በላይ ክልላዊና ሀገራዊ የለውጥ ሂደቱን በተሻለ ፍጥነት ወደፊት ለማራመድ የሚጠቅሙ ውሳኔዎች ማሳለፉ እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል ። እንደ አስተያየት ሰጪው ገለጻ ፓርቲው ብቃት ባላቸው አመራሮች መደራጀቱ በሀገሪቷ እውነተኛ ዴሞክራሲ ለማምጣት እየተሰራ ባለው ስራ ውስጥ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡ አዲሱ አመራርም ኃላፊነቱን በብቃት  በመወጣት ለህዝብ ያለውን አለኝታነት በተግባር ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል። ነባሮቹ አመራሮች ቦታቸውን ለአዲሶቹ ወጣት አመራሮች ማስረከባቸው ዴሞክራሲያዊ ባህሉ  እየጎለበተ መምጣቱን እንደሚያሳይ የገለጹት ሌላው የአምቦ ከተማ ነዋሪ መምህር አብዮት መንግስቱ ናቸው፡፡ ፓርቲው ስልጣንን በሰላማዊ መንገድ ማስረከብ እንደሚቻል ለሌሎች በተግባር በማሳየት አርአያነት ያለው ተግባር መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የጅማ ከተማ  ነዋሪው  ሼህ ኑሩ አባጀሃድ እንዳሉት ደግሞ የኦዴፓ ውሳኔዎች አካባቢያቸውን ብሎም ሀገሪቱን ጭምር የሚጠቅም ነው፤ ፓርቲው ከሁሉም በላይ ለሰላምና ለህግ የበላይነት መከበር መረባረብ አለበት። በተመሳሳይ ከመቱ ከተማ ነዋሪዎች መካከል  በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ አበራ ኃይሉ  በሰጡት አስተያየት   ፓርቲው በተግባር ያሳያቸው መልካም ውሳኔዎች በሌሎች የኢህአዴግ ደርጅቶች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ ይህም የሀገሪቱን መጪው እድል ብሩህ ሊያደርገው ይችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል። በፓርቲው የተደረጉት ማሻሻያዎች ያልተጠበቁ ግን ደግሞ አድናቆትን የጫሩና ተቀባይነት ያላቸው  እንደሆኑ የገለጹት ደግሞ በጉጂ ዞን ነገሌ ከተማ የቀበሌ ሶስት ነዋሪ አቶ ኢብራሂም አደም ናቸው፡፡ "በነባሮቹ ምትክ ወደ ኃላፊነት የመጡ አዲስ አመራሮች መልካሙን በመውረስ ህዝብን ሲያስለቅሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ ለሚያደርጉት ጥረት ተገቢው ድጋፍ እናደርጋለን" ብለዋል። በዞኑ ሊበን ወረዳ የሲሚንቶ ቀበሌ የሀገር ሽማግሌ አቶ ገርቡሌ ለጋ በበኩላቸው ኦዴፓ ያደረገው ለውጥ መልካም ቢሆንም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች  የህግ የበላይነት ባለመረጋገጡ እየተጎዱ ያሉትን ዜጎች ለመታደገ አዲሱ አመራር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባው ጠቁመዋል ። በፍቼ ከተማና አካባቢዋ የሚገኙ  የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው ለድርጅቱ ያላቸውንም አጋርነት  አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል ። በከተማው የሚኖሩት የህግ ባለሙያው አቶ ማሞ በላቸው  ድርጅቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በሃገሪቱ  ለተጀመረው  የመደመርና የአንድነት የለውጥ ጉዞ  ወሳኝ  እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ በሃገሪቱ ጎልተው  እየታዩ ያሉትን  ድህነት ፣የግጭትና ስራ አጥነትን ችግር   ለመፍታትም  ያለውን  ድርጅታዊ   ዝግጅነት  የሚያመላክት በመሆኑ  ለተፈፃሚነቱ  የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል፡፡ የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ  የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ  ሴኔሳ ነጋሹ በበኩላቸው ድርጅቱ  በጉባኤው ያካሄደው  ለውጥ  የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ  መሰረት የሚጥል በመሆኑ  እንደሚደግፉት  አመልክተዋል ። ድርጅቱ በተለይ ችግሮችን በእውቀትና በብልሃት  ለመፍታት ውሳኔው  የሚረዳው ከመሆኑም ባሻገር  ነባር አመራሮችን በክብር ማሰናበቱ ብቻ ሳይሆን  በወጣትና በአዲስ ኃይል መተካቱ  የሚጠቅም  መሆኑን ተናግረዋል ። የኦዴፓ  አባላትና አመራሩ አንድነታቸውን አጠንክረው  ከሕዝብ ጋር ተቀራርበው በጉባኤው ውሳኔ መሰረት  መስራት እንዳለባቸው ያመለከቱት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሙልጌታ ታዬ ናቸው፡፡ የክልሉ መንግስት የሚመራው ድርጅቱ ለወጣቶች የሰጠው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑን አመልክተው የአሁኑ ጉባኤም ወጣቱን  በሰፊው ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር የሴቶችን  ኑሮን ለማሻሻል አቅማቸውን አሟጠው ከድርጅቱ ጋር እንደሚሰሩ የተናገሩት የዞኑ ሴቶች ማህበር አባል ወይዘሮ   ጠጅቱ አረጋ   ናቸው፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ ፓርቲው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በመደገፍ በቀጣይ በሚያከናውናቸው ተግባራት ከጎኑ ሆነው የበኩላቸውን ለመወጣት  ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም