ቀጥታ፡

የአሸባሪውን ህወሃት ፕሮፖጋንዳ ከማክሸፍ ጎን ለጎን ለተጎዱ ወገኖች የምናደርገውን ድጋፍ እናጠናክራለን–የዳያስፖራ አባላት

ጥቅምት 1 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአሸባሪውን ህወሃት ፕሮፖጋንዳ ከማክሸፍ ጎን የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት ለሀገር የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ በአሜሪካ ሎስ አንጀለስና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተናገሩ።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በከተሞቹ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያይተዋል።

በእለቱ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ክስተቶች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ65ሺ ዶላር በላይ ድጋፍ ተሰባስቧል።

አምባሳደር ስለሺ በሀገራዊ ውቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ለተሳታፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

"ኢትዮጵያ ለህዝቧ የምትመች፣ ሰላም የሰፈነባትና አንድነቷ የተጠበቀ ሀገር ሆና እንድትቀጥል በመንግስት በኩል ሰፊ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው" ብለዋል።

በመንግስት በኩል ያለውን ቁርጠኛ የሰላም አቋም በመጻረር አሸባሪው ህወሃት ለሶስተኛ ጊዜ ወረራ በመፈጸም የቆየ የህዝብ ጠላትነቱን ማሳየቱን ተናግረዋል።

አምባሳደር ስለሺ የዳያስፖራ አባላት በቡድኑ የፕሮፖጋንዳ ክንፍ የሚነዛውን የሀገርን ስም የማጠልሸት ዘመቻና አፍራሽ ተግባር በተቀናጀ ጥረት የማክሸፍ ጥረት መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዲሞክራሲያዊ ስርዓት እና ተቋማት ግንባታ፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የግብርና ምርት ማሳደግ፣ ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅ ብሎም አዳዲሶችን በማስጀመር ረገድ አበረታች ውጤቶች መመዝገቡን አስረድተዋል።

በሎስ አንጅለስና አካባቢው ብሎም በመላው አሜሪካ የሚኖረው ዳያስፖራ እናት አገሩ ላቀረበችሁ ጥሪ ሁሉ ፈጥኖ በመድረስ ለሚያሳየው አለኝታነት ምስጋና አቅርበዋል።

በእለቱ በአገራችን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ክስተቶች ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከ65ሺ ዶላር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ተችሏል።

ተሳታፊዎቹ የህወሃትን ፕሮፖጋንዳ በማክሸፍና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በመርዳት የሚያደርጉትን ተግባር እንደሚገፉበት አስታውሰዋል።

ኤምባሲው ወቅቱን የሚመጥን በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት ሰፊ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም