ቀጥታ፡

የቴሌኮም ማጭበርበር የተደረገባቸው ህገ-ወጥ መሳሪያዎች ተያዙ

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2010 የቴሌኮም ማጭበርበር የተደረገባቸው ከ600 በላይ ህገ-ወጥ መሳሪያዎች መያዛቸውን ኢትዮ-ቴሌኮም አስታወቀ። ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ህገ-ወጥ የቴሌኮም ማጭበርበር ተግባር ላይ የተሳተፉ 70 ግለሰቦች መያዛቸውም ተገልጿል። የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አብዱራሂም አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች ይፈጸማሉ። የቴሌኮም ማጭበርበር ዓለም አቀፍ የድምጽ ጥሪዎችን በመቀነስ በአገሪቱ ገቢ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል ብለዋል። ኢትዮጵያ በህገ-ወጥ የቴሌኮም ማጭበርበር በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ከውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እያጣች ትገኛለች። በመሆኑም ይህን ህገ-ወጥ ተግባር ለመከላከል ግብረ-ኃይል መቋቋሙንና በቴክኖሎጂ የታገዘ የመከላከል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። አቶ አብዱራሂም ኩባንያው የአገልግሎት ጥራቱን በማሻሻልና ተደራሽ በማድረግ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም