ቀጥታ፡

በቴክኖሎጂ የታገዘ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሳይንስ ሙዚየምና የፈጠራ ስራዎች የላቀ ሚና አላቸው- የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች

ጥቅምት 01 ቀን 2015(ኢዜአ) በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣንና አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት የሳይንስ ሙዚየምና ሌሎችም የፈጠራ ስራዎች የላቀ ትርጉም ያላቸው መሆኑን የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን የሳይንስ ሙዚየም ጎብኝተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤ የሙዚየሙ ግንባታ እውን መሆን ኢትዮጵያ በፈተናዎችም ውስጥ ሆና የትኛውንም የልማት እቅድ ማሳካት እንደምትችል ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት እና የዘመኑ አሰራሮችን ለመከተል ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው፤ የሙዚየሙ መገንባት የአሁኑ ትውልድ ታሪክ ቀያሪ መሆኑን የሚያረጋግጥ አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ብልጽግና እንዲሁም የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑንም ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በበኩላቸው በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣንና አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት የሳይንስ ሙዚየምና ሌሎችም የፈጠራ ስራዎች የላቀ ሚና አላቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያን የሚያሳድጉ፣ የህዝቡን ኑሮ የሚለውጡ፣ እውቀትንና ገንዘብን ለማመንጨት የሚያስችሉ አስደናቂ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ  እንዳሉት ለኢትዮጵያ አቅም መሆን የሚችሉ አስደናቂ የፈጠራ ስራዎች በሙዚየሙ እየተሰሩ መሆኑ የሚያኮራ ነው።

የቴክኖሎጂ ዘርፉ በሚገባ ከተመራ የኢኮኖሚ ስርዓቱን በማሻሻል በኢትዮጵያ ሰፊውን የግብርና ልማት ጨምሮ ሌሎች ዘርፎችንም ለማዘመን የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች መበራከት ትልቅ ትርጉም አላቸው ብለዋል።

በሙዚየሙ እየተከናወኑ ያሉ የፈጠራ ስራዎችን በተለይም ወጣቶች እንዲጎበኙት በማድረግ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ያከናወነቻቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችም የአገሪቷን የፕሮጀክት አፈጻጸም የቀየረ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን አንስተዋል።

በሙዚየሙ የሚከናወኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችም ወጣቶች ተሞክሮ የሚቀስሙበትና ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።

የሳይንስ ሙዚየም የአሁኑ ትውልድ በጥረቱ የሚገነባትን የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑንም ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የግብርና፣ የደህንነት፣ የህክምና፣ የትምህርትና ሌሎች የልማት ስራዎች በማገዝ ወደ ቴክኖሎጂ የሚደረገውን ሽግግር በማገዝ ሙዚየሙ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የተገነባው የስነ ጥበብና የሳይንስ ሙዚየም በ7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ እና ሙሉ በሙሉ ከፀሐይ ብርሃን ኃይል እንዲያገኝ ሆኖ የተገነባ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም