ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዋጋ ተከፍሎበት የመጣው ለውጥ እንዳይቀለበስ የበኩሌን እወጣለሁ - ኢሕአፓ

አዲስ አበባ  መስከረም 12/2011 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በአገሪቱ የመጣው ለውጥ እንዳይቀለበስ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ  አስታወቀ። የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ሲገቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ተቀብለዋቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች አገር ውስጥ ገብተው በሠላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ የትጥቅ ትግልን የፖለቲካ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመብት ተከራካሪዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች ወደኢትዮጵያ በመምጣት ላይ ናቸው። በዛሬው እለትም ከ40 ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ በውጭ አገር ሲንቀሳቀሱ የቆዩ  የኢሕአፓ አመራሮች አዲስ አበባ ገብቷል። የፓርቲው ሊቀ-መንበር አቶ በላይነህ ንጋቱ በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን ለውጥ ኢሕአፓ የሚደግፈው መሆኑን ገልፀዋል። ''ለውጡ በከባድ መስዋዕትነት የመጣ ነው፤ ለውጡ ቀጣይነት ኖሮት መሰረት እንዲይዝ የሚጠበቅብንን ለማድረግ ዝግጁ ነን" ሲሉም አረጋግጠዋል። የፓርቲው ቃል አቀባይ ኢንጂነር ሰለሞን ገብረስላሴ በበኩላቸው "ያለንን የቆየ የፖለቲካ ተሞክሮ በመጠቀም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ ኃላፊነታችንን እንወጣለን" ብለዋል። ኢሕአፓ በኢትዮጵያ ያለውን አንድነት ለማጠናከርና የዜጎች መብቶችም እንዲከበሩ ለማድረግ ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ እንደሆነም ተናግረዋል። ''በተፈጠረው ምቹ የፖለቲካ ምህዳር በመጠቀም ፓርቲው ለማህበራዊ ፍትህ መታገሉን ይቀጥላል'' ያሉት ኢንጂነር ሰለሞን፤ በተለይም የህጻናትንና ጧሪ የሌላቸው አረጋዊያንን ህይወት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት መንግስትን ለማገዝ ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመዋል። የፓርቲው አመራር አባል አቶ መሐመድ ጀሚል በበኩላቸው ፓርቲው ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተግቶ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላቱ የቀይሽብር ሰማዕታት ሙዚየምን የጎበኙ ሲሆን በስፍራውም የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል። ኢሕአፓ የንጉሱ አገዛዝ መውደቅን ተከትሎ የተቋቋመ ሲሆን በተለይ በደርግ የመጀመሪያው ዓመታት በወታደራዊው መንግስት በተካሄደውና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በፈጀው የቀይ ሽብር ዘመቻ ሰለባ የሆነ የፖለቲካ ማህበር ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም