የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ክስተት የሆኑ የዕድሜ ባለጸጋ ተፈታኞች

19

መስከረም 30 ቀን 2015 (ኢዜአ) የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ላይ ከልጆቻቸው ጋር ለመፈተን ወደ መፈተኛ ማዕከላት የተገኙ የዕድሜ ባለጸጋዎች የፈተናው ክስተት ሆነዋል።

በዕድሜ የገፉት አባቶች አንዳንዶቹ ከልጆቻቸው ጋር አንዳንዶቹም ለብቻቸው ለመፈተን ወደ መፈተኛ ማዕከላት አቅንተዋል።

የእነዚህ አባቶች አኩሪ ተግባር በተለያየ ምክንያት ከትምህርት ርቀው ለነበሩና ወደ ትምህርት ለመመለስ ለሚያመነቱ ወጣቶች ከፍተኛ ትምህርት የሚሰጥ ከመሆኑም ባለፈ ከልብ ካለቀሱ እንደሚባለው ለመማር ምክንያት መደርደር ተገቢ አለመሆኑን አሳይቷል።

ፈተናውን ለመውሰድ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ከልጃቸው ጋር የተገኙት የ8 ልጆች አባት የሆኑት የ65 ዓመቱ አቶ አበራ ቦራ “መምህር የመሆን የልጅነት ህልሜን ለማሳካት ዝግጅት አድርጌ ለብሔራዊ ፈተናው ቀርቤያለው” ብለዋል።

መማር ኑሮን ከማሻሻሉ ባለፈ በራስ መተማመንን አጎልብቶልናል ያሉት ደግሞ ፈተናውን ለመፈተን በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የተገኙት አቶ ጌታሁን ክብረት እና የ70 ዓመት አዛውንቱ አቶ ከማል ኢሳ ይገኙበታል።

አቶ ጌታሁን ክብረት ኑሮዬን ለማሻሻልና እንደ ሰው ለመሆን በ50 ዓመቴ ዳግም ወደ ትምህርት ዓለም ተመልሼ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ከአንድ ልጄ ጋራ በጋራ እየወሰድን እንገኛለን ብለዋል።

ልጆቻቸውም "እኛ እንደተማርነው አንተም መማር አለብህ” በማለት ያቋረጡትን ትምህርት በ2011 ዓ.ም እንዳስጀመሯቸውና ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንዲቀርቡ እንዳደረጓቸው ተናግረዋል።

ከረጅም ዓመታት በኋላ ወደ ትምህርት ገበታ በመመለስ ለብሄራዊ ፈተና የተቀመጡት አቶ ጌታሁን ከራሳቸው አልፈው በቀጣይ ባለቤታቸውንም ለማስተማር ዕቅድ መያዛቸውን አውስተዋል።

ከ66 ዓመታት በኋላ ያቋረጡትን ትምህርት በ85 ዓመታቸው በድጋሚ በመጀመር ፈተናውን ለመውሰድ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የተገኙት አዛውንት አቶ ባፋ ባጋጃ “ዓላማዬ መማርና ለአገር በእውቀቴ ውለታ መዋል ነው” ይላሉ።

የስምንት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ባፋ በኑሮ ችግር ምክንያት ልጆቻውን አስተምረው ለቁም ነገር ለማብቃት ሲሉ በ1949 ዓ.ም ከ7ኛ ክፍል ማቋረጣቸውን አስታውሰው፤ ምንም እንኳን ዕድሜዬ ቢገፋም በትምህርት ላይ ያለኝን ቁጭት ለመወጣት ለመፈተን መጥቻለሁ ብለዋል።

ሌላኛው የዕድሜ ባለጸጋ አቶ አብደላ ሙሜ ሲሆኑ በ1983 ዓ.ም ያቋረጡትን የ8ኛ ክፍል ትምህርት በ2010 ዓ.ም መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

አቶ አብደላ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታቸው ትምህርታቸውን በአግባቡ እንደተከታተሉ በመጠቆም፤ ዘንድሮም ከሁለት ልጆቻቸው ጋር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያን እየወሰዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከትምህርትም ሂሳብንና እንግሊዘኛን አብልጠው እንደሚወዱ የተናገሩት አቶ አብደላ፤ መማር ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ትንሽ ትልቁ ትምህርትን በአግባቡ መማርና ማጠናቀቅ ይገባል ሲሉ ለትውልዱ ምክር ለግሰዋል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፈተናቸውን ለመውሰድ የተገኙት የዕድሜ ባለጸጋ አቶ አብደላ ሙሜ፣ አቶ ከማል ኢሳ እና አቶ ጌታሁን ክብረት ሲሆኑ፤ አቶ አበራ ቦራ በዲላ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም አቶ ባፋ ባጋጃ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለመፈተን የተገኙ አርዓያ የሆኑ አባቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም