ሀዋሳ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ 3 ነጥብ አግኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
ሀዋሳ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ 3 ነጥብ አግኝቷል
መስከረም 30/ 2015 (ኢዜአ) ሀዋሳ ከተማ በ2015 ዓ.ም የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ አሳክቷል።
ዛሬ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሁለተኛ ሳምንት ፕሪሚየር ሊግ መርሐግብር የመጨረሻ ጨዋታ ተደርጓል።
ሀዋሳ ከተማ አብዱልባሲጥ ከማልና ተባረክ ሄፋሞ ባስቆጠራቸው ግቦች ኢትዮጵያ ቡናን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ብሩክ በየነ ለቡናማዎቹ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ በሊጉ የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ በሁለት ጨዋታዎች ያገኘው ነጥብ አንድ ብቻ ነው።
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ቅዱስ ጊዮርጊስና ወልቂጤ ከተማ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን ይዘዋል።
የፕሪሚየር ሊጉ የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ይካሄዳሉ።
የዘንድሮው ሊግ የመጀመሪያ ዙር መርሐ ግብሮች በባህር ዳር ስታዲየም(ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ሳምንት)፣በድሬዳዋ ስታዲየም (ከስድስተኛ እስከ 10ኛ ሳምንት) እንዲሁም በአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርስቲ ሜዳ(ከ11ኛ እስከ 15ኛ ሳምንት) ይከናወናሉ።