ቀጥታ፡

የአገራዊ ምክክሩን ፋይዳ በጥልቀት በመገንዘብ የህዝቡ የላቀ ትብብርና ተሳትፎ እንዲኖር የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል

 መስከረም 30/2015 (ኢዜአ )  አገራዊ ምክክሩን ፋይዳ በጥልቀት በመገንዘብ የህዝቡ የላቀትብብርና ተሳትፎ እንዲኖር የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የማህበረሰብ ተወካዮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና የጋምቤላ ክልል ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል የተውጣጡ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ የሶስቱም ክልሎች የዞን አስተዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን የምክክር ኮሚሽኑ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ስኬት የድርሻቸውን ትብብርና እገዛ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ከተሳታፊዎቹ በአፋር ክልል የፈንተሪሱ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቢላል ዳርገዲሞ ፤በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የካማሺ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቢጂጋ ፃፊዮ ና በጋምቤላ ክልል የኑዌር ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቦስ ዳርበኢ እንዳሉት ትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የሚስተዋሉ አገራዊ ጉዳዮችን ወደ ጠረንጴዛ በማምጣት በንግግርና በምክክር በመፍታት ዘላቂ ሰላም መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በምንም አጋጣሚ የተከሰቱ ነገሮችን ለማረም መሆን ያለበት ''ቂምና ጥላቻን በተመሳሳይ ተግባር ምላሽ መስጠት ሳይሆን በፍቅርና ይቅርታ ማሸነፍ ይቻላል" የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ ምክክር የመፍትሔው አካል ይሆናል ነው ያሉት።

በመሆኑም የአገራዊ ምክክሩን ፋይዳ በጥልቀት በመገንዘብ የህዝቡ የላቀ ትብብርና ተሳትፎ  እንዲኖር የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አረአያ፤ አገራዊ የምክክር ሂደቱ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንድካሄድ የሁሉም ተሳትፎ ሊታከልበት ይገባል ብለዋል።

በዛሬው እለት ከአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልል የተውጣጡ የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር እየተካሄደ ያለው መድረክም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የህዝቡ የነቃ ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በቀጣይም ኮሚሽኑ ከሌሎች ክልል ተወካዮች ጋር መሰል ውይይቶችን የሚያካሂድ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው የውይይት መድረክ የሶስቱም ክልሎች የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችና ሌሎችም የማህበረሰብ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም