ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብርና ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

መስከረም 30/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብርና ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ የዲፕሎማሲ ስራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ስድስተኛ ዙር ሁለተኛ ዓመት አንደኛ የጋራ ስብስባ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል።

ፕሬዝዳንቷ የሁለቱን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ በይፋ የከፈቱ ሲሆን የበጀት ዓመቱ ዋና ዋና የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎችን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በ2014 በጀት ዓመት ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን የመሰረተ ልማት፣ የንግድና የህዝብ ለህዝብ የባህል ትስስር የሚያጠናክሩ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት ማከናወኗን ጠቅሰዋል።

የቀጣናውን አጠቃላይ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የዲፕሎማሲ አቅጣጫዎቿ የአካባቢውንና ጎረቤት አገራትን ለጋራ ጥቅምና ሰላም እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታን የፈጠረችበት ዓመት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የዓባይን ወንዝ ዘላቂ ጥቅም የሚፈልግ ሁሉ ለወንዙ ማሰብ ግድ ስለሚል ኢትዮጵያ ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ አስቀድማ በመረዳት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በትኩረት እየሰራችበት መሆኑን በማስታወስ።

ከዚህም ባሻገር ተሞክሮዋን በጎረቤት አገራት ለማስፋፋት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች መሆኗንም ጨምረው ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግብጽና ሱዳን በተመጣጣኝ ዋጋ ሃይል እንዲያገኙና ግድቡ የወንዙን ስነ ምህዳራዊ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

ከዚህ ቀደም በየወቅቱ የሚዋዥቀውን የወንዙን የውሃ መጠን በማስተካከል ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንዲኖር ያደርጋል ሲሉም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው እያስመዘገበች ያለው የልማት እመርታ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በዙሪያዋ ያሉ ጎረቤቶቿን በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚ በማድረግ ለአካባቢው ትብብርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጠናከር ቁርጠኝነቷን እያሳየች ትገኛለች ነው ያሉት።

በአዲሱ በጀት ዓመትም በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ጉልህ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት እንደሚከናወኑም አስታውቀዋል።

ለዚህም ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታን በአግባቡ በመገንዘበ ከጎረቤት እና ሌሎች ወዳጅ አገራት ጋር ያለውን ጠንካራ የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰራ አመላክተዋል።

ከዚህም ባለፈ የገፅታ ግንባታ ስራዎችና የውጭ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲያለሙ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም