ቀጥታ፡

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ በተረጋጋ ሁኔታ እንድንፈተን አስችሎናል-ተፈታኞች

መስከረም 30/2015 (ኢዜአ ) የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ በተረጋጋ ሁኔታ እንድንፈተን አስችሎናል ሲሉ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ገለጹ፡፡

የ2014 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ዛሬ መሰጠት ጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የፈተናውን አጀማመር በተመለከተ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ግቢ ተገኝቶ ቅኝት አድርጓል፡፡

በቅኝቱም ተፈታኝ ተማሪዎችንና የትምህርት ዩኒቨርሲቲውን የአስተዳደር ሰራተኞች አነጋግሯል፡፡

ከኢዜአ ጋር  ቆይታ ያደረጉ ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ መደረጉ ስለ ፈተና ሒደቱ በቂ ግንዛቤ እንድንይዝና ያለምንም መረበሽ እንድንፈተን አስችሎናል ብለዋል፡፡

በተለይ ደግሞ ፈተናው ከመድረሱ በፊት የነበረን ዝግጅት ዩኒቨርሲቲው ከፈጠረው ምቹ ሁኔታ ጋር ተደምሮ የራስ መተማመናቸውን ከፍ እንዳደረገላቸው ነው የተናገሩት፡፡

ተማሪዎች አክለውም ፈተናው በዚህ መልኩ መሰጠቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከመጡ ብዙ ተማሪዎች ጋር እንድንገናኝ እና ልምድ እንድንለዋወጥ እድል ፈጥሮልናል ብለዋል፡፡

ቀደም ብሎ ተገቢው ኦረንቴሽን ስለተሰጠን በምንፈተንበት ወቅት ምንም አይነት መደናገር አላጋጠመንም ነው ያሉት፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ የ12ኛ ክፍል ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ በትራንስፖርት ምክንያት ይፈጠር የነበረን መንጠባጠብ ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር ማድረጉንም እንዲሁ፡፡

የትምህርት ዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሽመልስ ዘውዴ በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያው ዙር 2 ሺህ 618 የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎችን እያስፈተነ ይገኛል ብለዋል፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንቱ በዛሬው እለት በጧቱ መርሃ ግብር የተከናወነውን ፈተና ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ አጠናቀዋል ነው ያሉት፡፡

አገር አቀፍ ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ ሌብነትን የሚጠየፍ እና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡

ዛሬ በተጀመረው የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ብሔራዊ ፈተና ከ560 ሺህ በላይ ተማሪዎች በ130 ማዕከላት  በተረጋጋና በሰላም እየወሰዱ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም