መንግስት የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የጀመራቸውን ጥረቶች ይገፋባቸዋል - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የጀመራቸውን ጥረቶች ይገፋባቸዋል - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
መስከረም 30 / 2015 (ኢዜአ) መንግስት የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የተጀመሩ ጥረቶችን በአዲሱም በጀት ዓመትም እንዲሚቀጥል የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
አሁንም የአፍሪካ ሕብረት ለሚያደርገውን የሰላም የጥረት መንግስት ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል ብለዋል።
6ኛው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን መክፈቻ ስነ-ስርዓት የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል።
በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የ2015 ዓ.ም ዋና ዋና የመንግስት አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ንግግር አድርገዋል።
መንግስት በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሬዝዳንቷ፤ መንግስት ከሕወሓት ጋር የሰላም ውይይት የማድረግ ጥረቱን እንደሚገፋበት ጠቁመዋል።
የሰላም ሂደቱን ለማስተጓጎል ለሚደረጉ ትንኮሳዎች መንግስት የማስታገሻ እርምጃ እንደሚወስድ ሊሰመርበት ይገባል ብለዋል።
በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አማካኝነት እየተደረገ ያለውን የሰላም ጥረት ስኬታማ እንዲሆን መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ከግጭት አዙሪት ወጥታ ዘለቄታዊ ሰላም እንድታገኝ ሁሉም ወገን የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ፕሬዝዳንቷ ጥሪ አቅርበዋል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሚያከናውነው ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ሁሉን አሳታፊ ያደረገ እንዲሆን አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።