ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ በሁሉም መስክ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል- አምባሳደር እሸቱ ጥላሁን

መስከረም 30/2015 (ኢዜአ ) የኢትዮጵያ የትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ በሁሉም መስክ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር እሸቱ ጥላሁን ተናገሩ።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማዕቀፍ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የትብብርና የጋራ የእድገት ማዕቀፍ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም ከጎረቤት አገሮች፣ አጠቃላይ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ እሳቤዎችን በመያዝ እየሰራች ትገኛለች።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር እሸቱ ጥላሁን፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ የትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ በሁሉም መስክ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሁሉም አገራት ጋር በትብብር የመሥራትና አብሮ የማደግ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ከጎረቤት አገራት ጋር የጀመረችው የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ትልቅ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሁሉም የዓለም አገራት ጋር አብሮ የመልማትና በጋራ የማደግ ፅኑ ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፤ ይህንኑ መሰረት ያደረገው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫ በተጠናከረ መልኩ ይተገበራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋሉ አንዳንድ ፍትሃዊ ያልሆኑ ምልከታዎችና የውጭ ጫናዎች ምንጫቸው ድህነት በመሆኑ ለዘላቂ ልማትና የልማት ትብብር በጋራ መሥራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል የወጣቶች ዘርፍ አስተባባሪ ማስተዋል ፋንታሁን፤ ኢትዮጵያ በተለይም ከአፍሪካ አገራት ጋር የአብሮነትና የልማት ትብብሯን የምታጠናክር መሆኑን ገልጻለች።

በተያዘው ዓመት ወጣቶች በስድስት የአፍሪካ አገራት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አንድ ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ጠቅሳለች፡፡

ከ54ቱም የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ወጣቶች በኢትዮጵያ ኮንፍረንስ የሚያካሂዱበት እቅድ መኖሩም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም