የህግ የበላይነት ለማስከበር በሚደረገው ጥረት አጋዥ ሚና እንደሚጫወቱ ፓርቲዎች ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
የህግ የበላይነት ለማስከበር በሚደረገው ጥረት አጋዥ ሚና እንደሚጫወቱ ፓርቲዎች ገለፁ
አዲስ አበባ መስከረም 12/2011 በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አጋዥ ሚና እንደሚጫወቱ ፓርቲዎች ገለፁ። ፓርቲዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የህግ የበላይነት ሙሉ ለሙሉ ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ሚናቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ በመንግስት በኩል እንዲፈጠር ጠይቀዋል። በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው የህግ የበላይነት አለመከበር በአገሪቱ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኃብት ላይ ጉዳት እያስከተለ ስለመሆኑ ፓርቲዎቹ አንስተዋል። ከዚህ በተጨማሪ የዜጎች ተዘዋውረው የመስራትና የመኖር ህገ-መንግስታዊ መብት ተሟልቶ ባለመከበሩ በርካታ ዜጎች ለህይወት ማጣትና ለመፈናቀል ተዳርገዋል። ይህም የተከሰተው በአገሪቷ በየወቅቱ ህግ የሚጥሱ ወንጀለኞች ላይ አስተማሪ እርምጃ ባለመወሰዱ እንደሆነ ገልጸው ፤ በየወቅቱ በሚፈጸም የወንጀል ድርጊት ተመጣጣኝ ርምጃ አለመወሰዱ የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደፈጠረ ተናግረዋል። የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ በአገሪቷ የህግ የበላይነት ለማስከበር በሚደረግ ጥረት የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። “እኛ ሁሉ ጊዜ ስለ የህግ የበላይነት መከበር እንሰብካለን” ያሉት አቶ ግርማ አሁን የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል በፓርቲያቸው መዋቅርና አባላት በኩል የተለያዩ ተግባራት እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ወንድወሰን ተሾመ በበኩላቸው በአገሪቷ የህግ የበላይነት ተሟልቶ ባለመከበሩ የበርካታ ዜጎች ህይወት ማለፍና ንብረት ውድመት ማስከተሉን ይናገራሉ። የህግ ጥሰቶች ለማስቆም የፖለቲካ ፓርቲዎች በምናደርጋቸው ህዝባዊ ሰልፎች፣ መግለጫዎችና እንቅስቃሴዎች የህግ የበላይነት የጠበቁ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ እንደተናገሩት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አጋዥ ሚና ለመጫወት ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ይገባል። የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት ዶክተር በዛብህ ደምሴ ''በአሁኑ ወቅት ችግር እየተፈጠረ ያለው መንግስት የዜጎች ደህንነት የማስከበር ግዴታውን በተገቢው መጠን ባለመወጣቱ ነው'' ሲሉ ገልጸዋል። የህግ የበላይነት ሙሉ ለሙሉ መከበር "ሁላችንም ያገባናል" ያሉት ዶክተር በዛብህ፤ መንግስት ጥናቶች እያካሄደ የዜጎች ደህንነት አደጋ ላይ ከመውደቁ በፊት አስቀድሞ እርምጃ መውሰድ እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል። ፓርቲዎቹ በሰጡት አስተያየት የህግ የበላይነት ካልተረጋገጠ በአሁኑ ወቅት እየታዩ ያሉ ችግሮች ከቁጥጥር ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።