ኮሚሽኑ ከአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና የጋምቤላ ክልል የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር እየመከረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ ከአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና የጋምቤላ ክልል የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር እየመከረ ነው
መስከረም 30 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአፋር፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ከጋምቤላ ክልሎች የህዝብ ተወካዮች ጋር እየተወያየ ይገኛል።
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንደገለፁት፤ በአገራዊ ምክክር ሒደት ውስጥ ሁሉም ክልልና ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እንዲሳተፉ ለማድረግ የተጠናከረ ተግባር እየተከናወነ ነው።
ኮሚሽኑ አገራዊ ምክክሩን በይፋ ከመጀመሩ በፊት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል።
በዛሬው እለትም ከአፋር፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ከጋምቤላ ክልሎች የህዝብ ተወካዮች ጋር ለሁለት ቀናት የሚቆይ የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የትኛውንም ተቃርኖና አለመግባባት ለመፍታት በርካታ እሴቶች ያሏት ሀገር መሆኗንም የተናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት የሁሉም ዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
ህዝቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ለህዝብ ቅርብ የሆኑ አካላት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ዛሬ ከሶስቱ ክልል የህዝብ ተወካዮች ጋር የሚደረገው የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረክም የዚሁ አላማ አንዱ አካል ነው ብለዋል።
ተወካዮቹ ስለ አገራዊ ምክክር አስፈላጊነትና ሂደት የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ በማንቃትና በማስገንዘብ ረገድ በሀላፊነት መስራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
በዋናነት በአገራዊ ምክክሩ ሁሉም የሚመለከተው አካል እንዲሳተፍ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ኮምሽነሩ አረጋግጠዋል።
ኮሚሽኑ ወደ ህዝቡ ወርዶ ከማወያየቱ በፊት ዛሬ የሚገኘው የሀሳብ ግብዓት በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በውይይት መድረኩ የሶስቱም ክልሎች የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጀቶች ተገኝተዋል።