በደባርቅ፣ እንጅባራ እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች ፈተናው በሰላም እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደባርቅ፣ እንጅባራ እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች ፈተናው በሰላም እየተሰጠ ነው
ባህር ዳር (ኢዜአ) መስከረም 30/2015 በደባርቅ፣ እንጅባራ እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች 37 ሺህ 311 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተናውን በሰላም እየወሰዱ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው አመራሮቹ አስታወቁ።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀጃው ደማሙ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን ለማስፈተን የሚያስችልውን ዝግጅት በማጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት 6ሺህ 750 ተማሪዎች ፈተናውን መውሰድ ጀምረዋል።
ፈተናው ያለምንም ችግር መስጠት መጀመሩን የገለጹት ዶክተር ጀጃው፣ የተፈታኝ ተማሪዎች ቁጥር በመብዛቱ ቤተመጻህፍትን ጭምር በመጠቀም ተማሪዎችን እያስፈተኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከሀገራዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በተለይም የተማሪዎች መኝታ፣ የመጠጥ ውሃ፣ የምግብና የጤና አገልግሎቶችን በተሟላ መልኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
በተደረገው ጠንካራ የቅድመ ዝግጅት ሥራም እስካሁን ያገጠመ ችግር አለመኖሩን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያው ዙር እንዲያስፈትን የተመደቡለትን 9ሺህ 661 ተማሪዎች ዛሬ ማስፈተን ጀምሯል።
የዩኒቨርሲቲው የህዝብና የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋ ታደሰ የ12ኛ ክፍል ፈተናው በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል
ዩኒቨርሲቲው በሁለት ዙር የፈተና መረሃ ግብሮች 15ሺህ 984 ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስፈትን ጠቅሰው፤ በመጀመሪያው ዙር የተቀበላቸው 9ሺህ 661 ተማሪዎች በአሁኑ ወቅት እየተፈተኑ መሆኑን ገልጽዋል።
"አስፈላጊ የሚባሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅም ፈተናው ያልምንም እንከን ተጀምሯል" ብለዋል።
ዳይሬክተሯ እንዳሉት፣ ፈተናው በዩኒቨርሲቲው በአግባቡ እንዲከናወን 283 ፈታኝ መምህራን፣ 27 የፈተና ጣቢያ ሃላፊዎችና የጸጥታ አካላት ተመድበው በተቀናጀ አግባብ እየሰሩ ነው።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛው ዙር የፈተና መረሃ-ግብር 6ሺህ 323 ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስፈትንም ታውቋል።
በተመሳሳይ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተቀበላቸው ከ20ሺህ 900 በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተናውን ያለችግር በሰላም እየወሰዱ መሆኑን አስታውቋል።
ዩኒቨርሲቲው በሁለት ዙር የፈተና መርሃ ግብሮች 37 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን እንደሚያስፈትን ተገልጿል።