የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንብን የጣሱ ከ1 ሺህ በላይ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ እርምጃ ወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንብን የጣሱ ከ1 ሺህ በላይ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ እርምጃ ወሰደ
መስከረም 29/2015 /ኢዜአ/የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት ደንብን የጣሱ ከ1 ሺህ በላይ በሚሆኑ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን ገለጸ።
አገልግሎቱ ደንበኞቼን እያማረረ ነው ያለውን ሌብነትን ለመቀነስና ከሙስና የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረኩ ነው ብሏል።
የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ እንደገለጹት ደንበኞችን በሚያጉላሉ አመራሮችና ሰራተኞች ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ ጠንካራ ርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም ሌብነት፣ ብልሹ አሰራርና የዲስፕሊን ግድፈት ፈጽመው የተገኙት ላይ ከቃል ማስጠንቀቂያ እስከ ሥራ ማሰናበት እርምጃ መውሰዱን አቶ መላኩ ተናግረዋል።
በዚህም 1 ሺህ 50 አመራርና ሠራተኞች አስተዳደራዊ ርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 24ቱን ከኃላፊነት የማንሳትና 75ቱ ከሥራ መሰናበታቸውን ጠቅሰዋል።
አገልግሎቱ በዘረጋው የቅሬታ መቀበያ ሥርዓት በመረጃ የተደገፉ ጥቆማዎች ከደረሱት በኅብረት ሥምምነትና የሥራ አመራር መተዳደሪያ ደንብ መሠረት እርምጃዎችን የሚወስድ መሆኑን ጠቁመዋል።
አገልግሎቱ ብልሹ አሰራር እንዳይኖር ለመግታት ጥረት እያደረገ ቢሆንም ጥቂት አመራርና ሠራተኞች ከሕገወጥ ደላሎች ጋር በመመሳጠር ብረተሰቡን እያማረሩ ነው ብለዋል።
በዚህም ሆን ብሎ ኃይል በማቋረጥ ኅብረተሰቡ ገንዘብ እንዲያሰባስብና እንዲከፍል በማድረግ ኃይልን መልሶ የማገናኘት ህገወጥ ተግባር እየተፈጸመ ስለመሆኑ ጥቆማዎች እንደሚደርሷቸው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ አገልግሎቱ ጠንካራ ርምጃ መውሰዱን የሚቀጥል ሲሆን፤ ህብረተሰቡ የራሱን መብት በገንዘብ አሳልፎ መሸጥ የለበትም ብለዋል።
በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ ዝርፊያና ውድመት የሚደርሰው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሠራተኞች የደንብ ልብስ በለበሱ ዘራፊዎች መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኅብረተሰቡ ኃይል ሲቋረጥና አጠራጣሪ ነገር ሲገጥመው በ905 ነፃ የስልክ መስመር እንዲሁም በየክልሉ ባሉ ዲስትሪክቶችና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽሕፈት ቤቶች ጥቆማውን መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።