ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚጸናው በደማችን ብቻ ሳይሆን ከተረጂነት በመላቀቅ ጭምር ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

መስከረም 29/2015 /ኢዜአ/የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚጸናው በደማችን ብቻ ሳይሆን ከተረጂነት በመላቀቅ ጭምር ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

የ2015 ሀገር አቀፍ የበጋ መስኖ የስንዴ ልማት መርሀ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት  በሶማሌ ክልል ዛሬ ተጀምሯል።

በዚሁ ወቅት የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፤ በድርቅ ክፉኛ ተጎድቶ የነበረው የሶማሌ ክልል አሁን በአረንጓዴ ሰብል መሸፈኑ ትልቅ ድል መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በቆላማ አካባቢ የሚኖሩና በድርቅ የሚጠቁ ማህበሰረቦች አካባቢያቸውን የማልማት አቅም እንደሌላቸው ተደርጎ በሚወሰድ የተሳሳተ ግንዛቤ በሰፈራ ችግርን ለመፍታት ይሞከር እንደነበር ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን መንግስት የቆላማ አካባቢ ማህበረሰብ ሰፊ የመልማት ጸጋና አቅም እንዳለው በመገንዘብ ሰፋፊ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን የሶማሌ ክልል ስኬታማ ተግባራት ተምሳሌት ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ወደተግባር በመቀየር ሀገራችን ስትጠቀስበት የኖረችውን የርዳታ ስንዴ ታሪክ ለማስቀረት በቁርጠኝነት ተነስተናል ነው ያሉት።

በዚህም የህዝቡን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር ኢትዮጵያም ከተረጂነት ተላቅቃ ስንዴ ወደ ውጭ መላክ የምትችል ሀገር መሆኗን በተግባር ለዓለም ለማስገንዘብ እየተሰራ መሆኑን በመጠቆም።

ይህም ኢትዮጵያ በልጆቿ ብርቱ ጥረት ሉዓላዊነቷን አጽንታ መቀጠል እንደምትችል በተግባር ያሳያል ነው ያሉት።

ቀደምት ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ክብር፣ ሉዓላዊነትና ነጻነት በደማቸውና በአጥንታቸው አስከብረው ለአሁኑ ትውልድ ማስረከባቸውንም ጠቅሰዋል።

መንግስትና ህዝቡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አፅንቶ ለማስቀጠል ከተረጂነት መላቀቅ የግድ መሆኑን በመገንዘብ በምግብ ራስን የመቻል ወሳኝ እርምጃ ውስጥ ናቸው ብለዋል።

በተለይም አመራሩ  ከንግግር ባለፈ በተግባር አርዓያነት ያለው እርምጃ ውስጥ እንዲገባ በብልጽግና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስበሰባ ላይ አቅጣጫ መቀመጡን በማንሳት።

በ2015 ዓም በአገር አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 52 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማምረት እቅድ ተይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም