ነባር አመራሮች የኦሮሞን ህዝብ ትግል ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረዋል- የኦዴፓ አዲስ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
ነባር አመራሮች የኦሮሞን ህዝብ ትግል ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረዋል- የኦዴፓ አዲስ አመራሮች
ጅማ 12/2011 የኦሮሞን ህዝብ ትግል ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ነባር የድርጅቱ አመራሮች የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደነበር የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አዲስ አመራሮች ገለፁ። በጅማ ከተማ ሲካሄድ ቆይቶ ትላንት በተጠናቀቀው ዘጠነኛው የኦዴፓ ጉባኤ አዲስ አመራሮች ለነባር የድርጅቱ አመራሮች አድናቆትና ክብር ችረዋል ። የኦዴፓ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው የተመረጡት አቶ ታዬ ደንዳአ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ነባር አመራሮች የኦሮሞን ህዝብ ትግል ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ። "አመራሮቹ በገዳ ባህል መሰረት ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉንና እንደሚያማክሩን እምነቴ የጸና ነው" ብለዋል ። ሌላው አዲሱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ዶክተር ቢቂላ አሬሳ በበኩላቸው ነባር አመራሮች የኦሮሞን ህዝብ ትግል ወደ ላቀ ደረጃ ከማሸጋገር ባለፈ ለአገር ግንባታ ያበረከቱት አስተዋፆ ከፍተኛ እንደነበር አውስተዋል። በገዳ ባህል መሰረት አመራሮቹ በክብር ተሰናብተው በአዲስ አመራር መተካታቸው የድርጅቱን ዲሞክራሲያዊ ባህሪ አጉልቶ ያሳየ ተግባር ነው " ሲሉ አድናቆታቸውን ችረዋል ። "አገር ማለት ትውልድ እየተቀባበለ የሚመራትና የሚወራረሳት ናት" ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሮባ ቱርጬ ናቸው ። "ኦዴፓ በዘጠነኛው ጉባኤው ይህንን እውነታ ተግባራዊ በማድረግ ታሪካዊ ውሳኔዎችን አሳልፏል" ብለዋል። አዲሱ አመራር ከነባር አመራሮች የካበተ ልማድ በመቅሰም የህዝብና የሀገርን ጥቅም የሚያስከብር አኩሪ ተግባር እንደሚፈፅም እምነታቸው መሆኑን አቶ ሮባ አስታውቀዋል ። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 80 በመቶ የሚሆነውን ነባር አመራሩን በአዲስ ኃይል በመተካት ጉባኤውን ማጠናቀቁ ታውቋል።