በስንዴ ልማት እንደ ሀገር የተያዘውን ራዕይ ዕውን ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
በስንዴ ልማት እንደ ሀገር የተያዘውን ራዕይ ዕውን ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢንስቲትዩቱ
ሀዋሳ መስከረም 29/2015 (ኢዜአ) በስንዴ ልማት እንደ ሀገር የተያዘው ራዕይ ለማሳካት በቴክኖሎጂ በማስደገፍና የተሻሻሉ ዝሪያዎች በማቅረብ የማገዝ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለፀ ።
በኢንስቲትዩቱ የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል በስልጤ ዞን ሳንኩራ ወረዳ የግብርና ቴክኖሎጂና የተሻሻለ ዝርያ ለማስተዋወቅ ከ100 ሄክታር የአርሶ አደር ማሳ ላይ በኩታ ገጠም ያለማውን የዳቦ ስንዴ አስጎብኝቷል።
በኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ተመራማሪና የስንዴ ምርት ተመራማሪ ዶክተር አለማየሁ ዘመዴ ስንዴ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሚመረቱ ሰብሎች ዋነኛው ምርት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ችላ ወደ ውጭ በመላክና የኢኮኖሚ አቅሟን ለማሳደግ በዚህ ረገድ ራእይ መሰነቋንም አክለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ይህን ዕውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የማገዝ ብሔራዊ ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ ሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም የተሻሻሉ ዝርያዎችንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ወደ አርሶ አደሩ በማሰራጨት አሁን ላይ በዝናብ ወቅት በሄክታር 30 ኩንታል አካባቢ የሆነውን አማካይ ሀገራዊ የስንዴ ምርት 50 እና ከዚያ በላይ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ስንዴ በባህሪው ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚሻ፣ ለበሽታ ተጋላጭና ውስብስብ ችግሮች ያሉበት ሰብል እንደሆነ ጠቁመው ኢንስትቲዩቱ ከምርትና ምርታማነት ማሻሻል ባለፈ የዝናብ እጥረትንና በሽታን የሚቋቋሙ የተሸሻሉ ዝርያዎችን በየጊዜው የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ እንደ ሀገር ስንዴ እየለማ ቢሆንም ሁሉም አርሶ አደሮች ወጥ የሆነ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አለመኖሩን ጠቅሰው ይህንን ክፍተት ለመሙላት የሚመለከታቸው አካላት በርብርብ ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በኢንስቲትዩቱ የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርና ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ሙሉቀን ፊሊጶስ በበኩላቸው ማዕከሉ ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችንና ዝርያዎችን የማመንጨት፣ የብዜት ሥራ እና ለአርሶ አደሩ የማስተዋወቅ ሥራዎችን እንደ ተልዕኮ ወስዶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
የዘር አቅርቦት፣ ሙያዊ ድጋፍና ሥልጠና መስጠት እንዲሁም ሌሎች እገዛዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ በመስጠት በሀገራዊ የስንዴ ልማት ዕቅድ ላይ አሻራውን እያኖረ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡
ማዕከሉ ድጋፍ በሚያደርግባቸው አካባቢዎች ላይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ከሀገራዊ አማካይ ምርት በሄክታር ከ10 ኩንታል በላይ የምርት ልዩነት ማስመዝገብ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ሙሉቀን ገለፃ ሙሉ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው በኩታ ገጠም ቴክኖሎጂ የሚያለሙ አርሶ አደሮች ምርታማነታቸውን ከማሳደጋቸው ባለፈ ምርታቸውን ከብክለት በፀዳ መንገድ የመሰብሰብና የተሻለ የገበያ ትስስር የመፍጠር ምቹ ዕድል እያገኙ ነው ፡፡
በኩታ ገጠም ስንዴ እያለሙ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ አበበች ታደሰ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በኩታ ገጠም ስንዴ መዝራታቸውን ተናግረዋል ።
የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል ማሳቸውን በትራክተር ከማሳረስ ጀምሮ የዘር አቅርቦትና ሌሎች የቴክኖሎጂ ድጋፎችን እንዳደረገላቸው ገልፀዋል ።
ከዚህ በፊት በተበጣጠሰ ማሳችን ላይ በብተና ነበር የምንዘራው ያሉት አርሶ አደር አበበች፤ ከሌሎች ጋር ተባብረው በመስራታቸውና የመስመር ቴክኖሎጂ ተጠቅመው በመዝራታቸው አዝመራቸው ከዚህ በፊቱ በተሻለ ጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት ።
የኩታ ገጠም እርሻ ዘዴ በቀላል ወጪ ትራክተርና ኮምባይነር ለማግኘትና ምርታችንን በአንድ ጊዜ ለመሰብሰብ ያግዘናል ብለዋል ፡፡
አርሶ አደር ሰለሞን ታደሰ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ምርጥ ዘር ብንጠቀምም የምንዘራው ወጥ ባልሆነ መንገድ በየግላችን ማሳ ላይ ነበር ብለዋል ፡፡
የሰብሉ አይነትም የተለያየ እንደነበርና ለብክነት የሚያጋልጥ አሰራር እንደሆነ አስረድተዋል።
በተናጥል በሚያለሙበት ወቅት የነበረውን ዳተኝነትና ድካም በማስቀረትም ዘወትር በተጋት እንዲሰሩ ብሎም እንዲደጋገፉ ምክንያት የሆነላቸው አዲስ አሰራር መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
ማዕከሉ በማሳቸው ላይ ተግባራዊ አድርጎ ካሳያቸው የቴክኖኖጂ አጠቃቀም በቂ ተሞክሮ መቅሰማቸውን ገልፀው ከዚህ በኋላ የወሰድነውን ልምድ ተጠቅመን ለመዝራትና ምርታማነታችንን ለማሻሻል ዝግጁ ሆነናል ብለዋል ፡፡
በመስክ ምልከታው ላይ የኢንስትቲዩቱ የሥራ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች፣ የስልጤ ዞንና የሳንኩራ ወረዳ አመራሮች፣ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትና የአካባቢው አርሶ አደሮች ተገኝተዋል ፡፡