ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዘንድሮ ዓመት የስንዴ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ትጀምራለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

መስከረም 29 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በዘንድሮ ዓመት የስንዴ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደምትጀምር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የዘንድሮውን ዓመት የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት መርሀ ግብርን በሶማሌ ክልል ዛሬ አስጀምረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የድህነት ታሪክ የሚቀየረው በብርቱ ልጆቿ ያላሰለሰ ጥረት ነው።

ኢትዮጵያውያን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በስንዴ ልማት መርሃ ግብር በንቃት በመሳተፍ ከውጭ የእርዳታ ስንዴ ማስገባት ታሪክ ሆኖ እንዲቀር አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ በስንዴና ሌሎች የልማት መስኮች ስኬት ማስመዝገብ ብትችልም ካላት የመልማት አቅም አንፃር ግን አሁንም ብዙ መስራት ይጠይቃል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከፍተኛ አመራሮች ለስንዴ ልማት መርሃ ግብሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመት በሚሊዮን ኩንታል የሚቆጠር ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደምትጀምር ገልጸው፤ ለዚህ ስኬት በሁሉም የልማት መስክ ሌብነትን መታገል ይገባል ብለዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባ በስንዴ ልማት መርሃ ግብር ድህነት ታሪክ የሚሆንበት ውሳኔ ማሳለፉንም ጠቅሰዋል፡፡

በ2015 ዓም በአገር አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 52 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማምረት እቅድ ተይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም