በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ተሰበሰበ
መስከረም 29 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሕክምና የሚውል ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ተሰበሰበ።
የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ(ኢክናስ)፣ ‘ፒፕል ቱ ፒፕል’ እና ሄልዝ ኬር አሊያንስ ፎር ኢትዮጵያ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የበይነ መረብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ትናንት ማምሻውን ተካሄዷል።
በመርሐግብሩ ላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፣በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የዳያስፖራ ተቋማትና ጥምረት ኃላፊዎችና የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።
በገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱ ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ማሰባሰብ መቻሉን አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገልጸዋል።
አምባሳደሩ መርሐግብሩን ላዘጋጁና ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ለወገናቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢክናስ፣ ‘ፒፕል ቱ ፒፕል’ እና ሄልዝ ኬር አሊያንስ ፎር ኢትዮጵያ በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ለተጎዱ ሁለት ሺህ ዜጎች 400 ሺህ ዶላር ለማሰባሰብ እቅድ መያዛቸው ተገልጿል።
የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን ለማግኘት የመጀመሪያው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ትናንት ማምሻውን መካሄዱንና ሶስቱ ተቋማት ያቀዱትን ገንዘብ ለማግኘት ተከታታይ ስራዎች እንደሚያከናውኑ ኢዜአ ከኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ(ኢክናስ) ያገኘው መረጃ ያመለክታል።