ቀጥታ፡

የሳይንስ ሙዚየም በአፍሪካ ላይ የሚሰነዘሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን የሚቀይር ነው--አፍሪካውያን ጋዜጠኞች

መስከረም 28/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም አፍሪካን በመጥፎ ገፅታ የሚያነሱ የተሳሳቱ ትርክቶችን የሚቀይር መሆኑን ሙዚየሙን የጎበኙ አፍሪካውያን ጋዜጠኞች ተናገሩ።

ከጋና፣ ካሜሮን፣ ኒጀር፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳና ሌሎች ሀገራት የተውጣጡ የአፍሪካን ገፅታ ለመገንባት የተቋቋመው የአፍሪካ ህብረት የሚዲያ ቡድን አባላት የሆኑ ጋዜጠኞች የኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየምን ጎብኝተዋል።

በሙዚየሙ ውስጥ ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለአፍሪካ እድገት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የሳይንስና ፈጠራ ስራዎችን መመልከታቸውን ከጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

ከሩዋንዳ የመጣው ጆንሰን ካናሙጂሬ የኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም አፍሪካ በሳይንስና ቴክኖሎጂው መስክ አሁን ያለችበትንና ልትደርስበት የተለመችውን ደረጃ የሚያሳይ መሆኑን ገልጿል።

አፍሪካ ከሌሎች ጥገኝነት ተላቅቋ በራሷ ሳይንቲስቶች ወደ እድገትና ብልጽግና መራመድ የምትችልባቸው የሳይንስ ፈጠራ ውጤቶች ማፍለቅ መጀመሯን በሙዚየሙ ውስጥ መመልከቱን ጠቅሷል።

የሳይንስ ሙዚየሙ አፍሪካን የግጭት፣ የድህነትና የኋላቀርነት አህጉር እንደሆነች ተደርጎ የሚቀርበውን የተሳሳተ ትርክት በመቀየር አህጉሪቱ የተስፋ ጎህ እየፈነጠቀባት የምትገኝ ስለመሆኗ ምስክር ነው ብሏል።

በቀጣይ እንደ አንድ አፍሪካዊ ጋዜጣኛና ጸሐፊ አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ የመፍታት ጥበቡም አቅሙም እንዳላት በዘገባዎቹ አጉልቶ እንደሚያሳይ ነው የተናገረው።

ደቡብ አፍሪካዊው ጋዜጠኛ ሲሚ አረፍ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የሚያግዙ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶችን በሙዚየሙ መመልከቱን ገልጿል።

ይህ የኢትዮጵያ ተሞክሮ አህጉራዊ መሆን እንደሚገባው ጠቅሶ፤ አፍሪካ በሳይንስና በሌሎች ዘርፎች እያስመዘገበች ያለውን ስኬት አጉልቶ ለዓለም ለማሳየት ሙዚየሙን በተምሳሌትነቱ እንደሚጠቅስ ናግሯል።

የአፍሪካ ህብረት የኮሙዩኒኬሽን ሃላፊ ውይኒ ሙሳባያና በበኩላቸው "ሙዚየሙ ለአፍሪካውያን ዓይን ገላጭ ነው" ብለዋል።

ዓለም በአፍሪካ ላይ ያለውን የተሳሳተ ትርክት ለማስተካከልና የአፍሪካ ህብረት ለሚሰራው የተግባቦት ስራም የኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑንም አክለዋል።

በቴክኖሎጂና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የቀረቡ የፈጠራ ውጤቶች አፍሪካ ለችግሮቿ መፍትሄ ማምጣት የምትችል አህጉር መሆኗን ጋዜጠኞቹ በማሳያነት ወስደው በትኩረት የሚሰሩበት ይሆናል ነው ያሉት ሃላፊዋ።

በሌላ በኩል ጋዜጠኞቹ የአንድነት ፓርክን የጎበኙ ሲሆን በፓርኩ ውስጥ ለቱሪስት መስህብ የሚሆኑ በርካታ ያልተነገሩ ታሪኮች መኖራቸውን ተመልክተናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም