የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የአገልግሎት ፍጥነትና የደህንነት ችግሮችን በመቀነስ ትርፋማነቱ ማደጉን አስታወቀ

መስከረም 27 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የአገልግሎት የፍጥነትና የደህንነት ችግሮችን በመቀነስ ትርፋማነቱ ማደጉን አስታወቀ ።

ድርጅቱ “ፖስታ ለፕላኔታችን“ በሚል መሪ ሃሳብ የፊታችን እሁድ የሚከበረውን ዓለም ማቀፍ የፖስታ ቀን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሀና አርዓያሥላሴ፤ በመግለጫቸው ድርጅቱ የዓለም ፖስታ ቀንን ምክንያት በማድረግ "ፖስታ ትላንት፣ ዛሬና ነገ" በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 1 እስከ 4 በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ብለዋል።

በዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት የ128 ዓመታት ባለታሪኩ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የፍጥነትና የደህንነት ችግሮችን ለመቀነስ ባከናዎናቸው ስራዎች ከኪሳራ ወደ ትርፋማነት መሸጋገሩን አስታውሰዋል።

በ2012 ዓ.ም አፈጻጸሙ ጥቅል ገቢውም ሆነ የተጣራ ትርፉ ኪሳራ እንደነበር አስታውሰው፤ በ2013 ከታክስ በፊት 72 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገልጸዋል።

በ2014 በጀት ዓመት ደግሞ በ2013 በጀት ዓመት የነበረውን 450 ሚሊየን ዓመታዊ ገቢውን በዕጥፍ በማሳደግ 907 ሚሊየን ብር ሲያደርስ፣ 187 ሚሊየን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ተናግረዋል።

በ2015 በጀት ዓመት አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢውን ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በማሳደግ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ  የተጣራ ትርፍ ለመሰብሰብ ማቀዱን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ከ700 ቅርንጫፎች በተጨማሪ ከሌሎች አካላት ጋር በውክልና ለመስራት የሚያስችል አሰራር ዘርግቶ ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።

የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ከሚሰጡ 168 አገራት መካከል በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2020 ከነበረበት 117ኛ ደረጃ በ2021 ወደ 34ኛ ደረጃ በማሻሻል ፈጣን ዕድገት ማሳየቱን አንስተዋል።

ከአገልግሎት ፍጥነትና የመልዕክቶች ደህንነት ዙሪያ የነበሩበትን ችግሮች ለማቃለል ዘመናዊ የደህንነት ካሜራዎችን  መግጠምን ጨምሮ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰዱን ተናግረዋል።

በ2014 በጀት ዓመት ድርጅቱ ካስተናገዳቸው 7 ነጥብ 4 ሚሊየን ዕቃዎች መካከል 36 ዕቃዎች ላይ የመልዕክት ደህንነት ችግር መስተዋሉን ጠቅሰው፤ ያጋጠሙ ችግሮችም የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዓለም የፖስታ ቀን ከ4000 ቴምብሮች የሚቀርቡበት ዐውደ ርዕዮች፣ የተማሪዎች ደብዳቤ አፃፃፍ ውድድሮች፣ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና በሌሎች ዝግጅቶች ያከብራል።

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት በ1901 ዓ.ም የዓለም ፓስታ ኅብረትን በመቀላቀል ከቀዳሚዎቹ አባል ድርጅት ተርታ የተሰለፈ ነው።

ድርጅቱ የፖስታ፣ የፈጣን መልዕክት፣ ሎጀስቲክስ፣ መንግስታዊ አገልግሎት፣ የፋይናንስ አገልግሎት፣ የፖስታ ሙዚየምና ፖስታ መደብር ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም