የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር 512 ከምዕራብ ሀረርጌ ዞን የተውጣጡ የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎችን ወደ ድሬደዋ ዩኒቨርስቲ በማጓጓዝ ላይ ነው

ጭሮ/ጊምቢ መስከረም 27 ቀን 2015 ዓ.ም ---የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር 512 ከምዕራብ ሀረርጌ ዞን የተውጣጡ የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎችን ወደ ድሬደዋ ዩኒቨርስቲ በማጓጓዝ ላይ ነው።

ተማሪዎቹ ከሚኤሶ ባቡር ጣቢያ በተሸኙበት ወቅት የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ፤ አክሲዮን ማሕበሩ አገራዊ ኃላፊነቱን የተወጣበት ነው ብለዋል።

የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር የሕዝብ ንብረት እንደመሆኑ ተማሪዎች ያለምንም መጉላላት ወደሚፈተኑበት ዩኒቨርሲቲ ለማድረስ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተፈታኝ ተማሪዎች በባቡር እንዲጓዙ መደረጉ ወጪ፣ ጊዜና ጉልበታቸውን ቆጥበው ተረጋግተው ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲደርሱ ነው ብለዋል።

ተማሪዎች ተረጋግተው ፈተናቸውን በመውሰድ ለአገርና ሕዝብ የሚጠቅሙ ዜጎች መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ተፈታኝ ተማሪዎችም በዚህ መልኩ ፈተና በመውሰድ የመጀመሪያ በመሆናቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

በመሆኑም ፈተናቸውን ተረጋግተው በመውሰድ ጠንክረው አገራቸውን በእውቀታቸው ለማገለግል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ለሚጓዙ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሽኝት ተደረገላቸዋል።

ከዞኑ ወረዳዎችና ከተማዎች የተውጣጡ ከ42 ሺህ በላይ ተማሪዎች የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ለመውሰድ መመዝገባቸውን የዞኑ ትምህርት ቤቶች ምክትል ሃላፊ አቶ ጌታቾ ቀበና ተናግረዋል፡፡

ከነዚህ መካከል ከ26 ሺህ 426 የማሕበራዊ ሳይንስ ተፋተኝ መሆናቸውን ተናግረው 15 ሺህ 299 ተማሪዎች ደግሞ የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኝ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ተማሪዎቹም ፈተናውን የሚወስዱትም በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ጊቢና አሶሳ ዩኒቨርሲቲ መሆኑም ታውቋል።

የተሸኙ ተማሪዎችም በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆነው አገር አቀፍ ፈተና ለመውሰድ መዘጋጃታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም