ቀጥታ፡

ወጣት ማዕከላቱ ለሶስት ዓመታት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2010 በአዲስ አበባ ሶስት ወጣት ማዕከላት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ከሶስት ዓመት በፊት ክፍያ ቢፈጸምም እስካሁን አገልግሎቱን ማግኘት አልቻሉም። የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ማዕከላቱ ለወጣቱ የስብዕና መገንቢያ ተብለው ቢቋቋሙም አንዳንዶቹ በመሰረተ ልማት ችግር የሚፈለገውን አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም ብሏል። በቢሮው የወጣት ማዕከላት አገልግሎት ማስፋት ድጋፍና ክትትል ቡድን መሪ አቶ ደረጀ ተስፋዬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት መንግስት የወጣቱን ስብዕና ለመገንባት በከተማዋ የወጣት ማዕከላት ገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። አብዛኞቹ ማዕከላት መሰረተ ልማቶቻቸው ተሟልተው አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም  አንዳንዶቹ ላይ ግን ችግሩ በስፋት ይስተዋላል። ለአብነትም የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ከሶስት ዓመታት በፊት ክፍያ የተፈጸመባቸው ሶስት የወጣት ማዕከላት እስካሁን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። እንደ ኃላፊው ገለጻ ወረዳዎችም ሆነ ክፍለ ከተሞች ለሚመለከተው አካል ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ቢያቀርቡም ወረፋ ጠብቁ ከሚል ምላሽ የዘለለ መፍትሄ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል። እነዚህ ማዕከላት ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው ወጣቱ አልባሌ ቦታ እንዳይውል የአይ ሲ ቲ፣ የካፍቴሪያ፣ የጂምናዚየምና የዲኤስ ቲቪ አገልግሎት ለመስጠት ቢቋቋሙም የሚጠበቀውን አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡ በዚህም በማዕከላቱ በስራ ዕድል ፈጠራና በስብዕና ግንባታ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ አለመቻላቸውን ነው ችግሩ ያጋጠማቸው የወጣት ማዕከሎች ስራ አስኪያጆችና ባለሙያዎች የሚናገሩት። በጉለሌ ክፍለከተማ የወረዳ አንድ ወጣት ማዕከል የቤተ መጽሃፍት ባለሙያ ወይዘሮ ዮዲት ጉልላት "ወጣት ማዕከሉ ስምንት አይነት አገልግሎቶችን ይሰጣል ተብሎ ይታሰባል አሁን ቢያንስ ግማሾቹን እየተሰጠ አይደለም ብለዋል፡፡ የማዕከሉ ጅምናዚየም ፤ ካፍቴሪያ ፡ አይ ሲ ቲ እየሰራ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል። በአራዳ ክፍለክፍለ ከተማ የወረዳ 10 ወጣት ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ ታረቀኝ በበኩላቸው "መብራት ባለመኖሩ ሳቢያ አይሲቲ ሩም እንደማይሰራና በአግባቡ መጠቀም እንዳልተቻለ ተናግራል፡፡ ለኤሌክትሪክ አገልግሎት መስሪያ ቤት ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ቢያቀርቡም ምላሽ ሊሰጣቸው አለመቻሉንም ነው የጠቆሙት። በመሆኑም ችግሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሚያስነሳና ለብልሹ አሰራር የሚያጋልጥ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። በጉዳዩ ላይ ኢዜአ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ምላሽ አላገኘም። ተቋሙ በጉዳዩ ላይ ምላሽ መስጠት በሚችልበት ጊዜ የምናስተናግድ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም