የክህሎት ስልጠናን ገበያ መር ለማድረግ አዲስ የስልጠና ስርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የክህሎት ስልጠናን ገበያ መር ለማድረግ አዲስ የስልጠና ስርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱ ተገለጸ
አዳማ መስከረም 27/2015. /ኢዜአ/ የክህሎት ስልጠናን ገበያ መር ለማድረግ አዲስ ስልጠና የስርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ከኦሮሚያ፣ ጋምቤላና አፋር ክልሎች ለተወጣጡ የቴክኒክ ሙያ ኮልጆች፣ የኢንዱስትሪ ሰላምና ስራ ስምሪት፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ሴክተሮች ሙያተኞችና አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና በአዳማ በመስጠት ላይ ይገኛል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለፁት ሁሉም የስልጠና ፕሮግራሞች የኢንዱስትሪ ገበያው የሚፈልጋቸው መሆን አለባቸው ብለዋል።
በተለይ በቁ ተወዳዳሪና በክህሎት የበቃ የሰው ሃይል ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለማቅረብና ለስራ ዕድል ፈጠራ ስልጠናው ጉልህ ሚና እንዲኖረው ለማስቻል እየሰሩ መሆኑን ገልጿል።
ከስራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር በገበያ ትስስርና ሙያዊ ክህሎት በማዳበር ረገድ አዲሱ የስልጠና ስርዓተ ትምህርት የላቀ ድርሻ አለው ብለዋል።
በተጨማሪም የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ዙሪያ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለፁት አቶ አሰግድ በተለይ በዘርፉ የሚሰማሩ ዜጎች ሙያው በሚፈልገው ስልጠና እጃቸው የተፍታታና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ክህሎትና የሙያዊ ዕውቀት እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑን ተናግሯል።
በተጨማሪም የሰለጠኑ ሙያተኞች በውጭ ሀገር ስራ እንዲሰማሩ ለማስቻል ሰፊ ስራዎችን እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዘንድሮው ዓመት 3 ነጥብ 7 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን የገለፁት አቶ አሰግድ በመስሪያና መሸጫ ቦታዎች፣ የብድር አገልግሎት የማመቻቸት ስራ ላይ ከክልሎች ጋር የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አመልክቷል።
የክህሎት ስልጠናን ገበያ መር ለማድረግ የኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ገበያን መሰረት ያደረጉ ጥናቶች መካሄዱን የገለፁት ደግሞ በሚኒስቴሩ የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ መነን መለስ ናቸው።
ጥናቱን መሰረት በማድረግ አሁናዊና የቀጣይ 10 ዓመት የሀገሪቷ የልማትና ዕድገት ጉዞን ታሳቢ ያደረገ አዲስ የክህሎትና ስልጠና ስርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የክህሎት ስልጠና ኮሌጆች በአካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተቆራኘ አደረጃጀት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ወጥ የሆነ የሙያና የክህሎት ስልጠና ይሰጣል ብለዋል።
የተቀናጀ የክህሎት ልማት፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ትስስርና ደህንነት ለማጠናከር ከተለመደው የስልጠና ስርዓትና አሰራር ለመውጣት ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።