ውሃ በማይገኝበት አካባቢ የተሰራው የውሃ ማጠራቀሚያ /ቢርካ/ እኛን ከእንግልት እንስሳቶቻችንን ከሞት ታድጎልናል -- በሶማሌ ክልል ነዋሪዎች

75

መስከረም 27 / 2015 (ኢዜአ)  በሶማሌ ክልል እፍኝ ውሃ በማይገኝባቸው አካባቢዎች የተሰራው የውሃ ማጠራቀሚያ /ቢርካ/ እኛን ከእንግልት እንስሳቶቻችንን ከሞት ታድጎልናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሉ አርብቶ አደሮች ገለጹ።

የውሃ ማጠራቀሚያው እንዲሁም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ዜጎችን ከመፈናቀል እንስሳትን ከሞት እየታደገ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ድርቅ ከሚያጠቃቸው ቦታዎች መካከል የሚጠቀሰው የሶማሌ ክልል ጎርፍ፣ ድንበር ተሻጋሪ በሽታ (ወረርሽኝ)፣ ግጭትና ሌሎችም እየፈተኑት ይገኛሉ።

የሶማሌ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክትል ቢሮ ኃላፊ አብዱልፈታህ አብዱ መሀመድ፤ ከአራት ዓመታት በፊት በነበሩ ግጭቶች ፣ በድርቅና በደራሽ ጎርፍ ከተፈናቀሉ ዜጎች መካከል ከ550 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

በፌደራልና በክልሉ መንግስት እንዲሁም በአጋር አካላት ትብብር በተሰራው የአደጋ ስጋት ቅነሳ በርካታ አደጋ አንዣቦባቸው የነበሩ ዜጎች መደበኛ ህይወታቸውን መምራት የሚችሉበት እድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

በክልሉ በተለይም በፋፈን፣ ጀረርና ሸበሌ ዞኖች ህብረተሰቡን በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በጤና ተቋማት ግንባታ፣ በመስኖ ልማትና በውሃ ማጠራቀሚያ ቢርካ ግንባታ በማሳተፍ ከአደጋ ስጋት እንዲወጡ ተደርጓል ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ከፊል አርብቶ አደሮች መንግስት በአካባቢው የነበረውን ድርቅና ጎርፍ አደጋ ታሳቢ በማድረግ በሰራው የውሃ ማጠራቀሚያ /ቢርካ/ እና የአካባቢ ጥበቃ ስራ በቀያችን ሆነን ማልማት ጀምረናል ብለዋል፡፡

በፋፈን ዞን ሸበሌይ ወረዳ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው የውሃ ማጠራቀሚያ ከመሰራቱ በፊት ውሃ ለመቅዳት እስከ 15 ኪሎ ሜትር በእግራቸው ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የውሃ ማጠራቀሚያው ከተሰራ በኋላ ከብቶቻቸውን ከማጠጣትና ለቤት ውስጥ ፍጆታ ከማዋላቸው በተጨማሪ የጓሮ አትክልት ለማልማት እየተጠቀምንበት ነው ብለዋል፡፡

በአደጋ ስጋት ቅነሳ መርሃ ግብር "እፍኝ ውሃ በማይገኝበት ቦታ የተሰራው የውሃ ማጠራቀሚያ/ቢርካ/ እኛን ከእንግልት እንስሳቶቻችንን ከሞት ታድጎልናል" ብለዋል፡፡

በቀጣይም በአካባቢው ያለውን የህዝብ ቁጥር ታሳቢ በማድረግ ተጨማሪ የውሃ ማጠራቀሚያ ቢርካ እንዲሰራላቸው ጠይቀዋል፡፡

በሶማሌ ክልል የአደጋ ቅነሳና መልሶ ማቋቋም  ፕሮጀክት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሄኖክ በየነ፤ በሶማሌ ክልል ከ60 በላይ ወረዳዎች "የወረዳ አደጋ ቅነሳ ዕቅድ" ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ገብተናል ብለዋል፡፡

በዚህም በክልሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ በመስራት፣ አዳዲስ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን በመገንባትና የተበላሹትን በመጠገን በዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ቀድሞ መከላከል ተችሏል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም