የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠገን የተደረገው ጥናት በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል- የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ

232

መስከረም 27 /20215 (ኢዜአ) የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠገን እየተከናወነ ያለው ጥናት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።

የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን የሚያስቃኝ አውደ ርዕይ ''ላሊይበላ፤ በእምነት የታነጸ'' በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እንጦጦ ፓርክ ተከፍቷል።

May be an image of 6 people and people standing

አውደ ርዕዩ በቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የፈረንሳይ መንግሥት እንዲሁም የቅዱስ ላልይበላ ደብር ጽህፈት ቤት በጋራ የተዘጋጀ ነው።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እና በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሾ አውደ ርዕዩን በይፋ ከፍተውታል።

በአውደ-ርዕዩም የቤተክርስቲያኑ ታሪክ /በቨርቹዋል ሪያሊቲ/ ቴክኖሎጂ ጭምር ለእይታ የቀረበና ለሁለት ወራት የሚቆይ እንደሆነ ታውቋል።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በኢትዮጵያ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን በቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ ላይ ሰፊ ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።

የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ታሪክ ለማስተዋወቅ የተከፈተው አውደ ርዕይ የዚህ አንዱ አካል ሲሆን በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የቨርቹዋል ሪያሊቲ አውደ ርዕይ ሁሉም እንዲመለከተው ጋብዘዋል።

May be an image of outdoors

በኢትዮጵያ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን በቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ ላይ እቅድ የተያዘ ሲሆን ዛሬ የተከፈተው ቨርቹዋል ሪያሊቲ አውደ ርዕይ የእቅዱ አካል መሆኑንም ተናግረዋል።

የፈረንሳይ መንግስት ባለፉት ሶስት ዓመታት አብያተ ክርስቲያናቱን ለመጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ሲደግፍ መቆየቱንም አንስተዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋባዥነት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን መጎብኘታቸው አስታውሰዋል።

በፈረንሳይ መንግስት ድጋፍ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን የጥገና ስራ ለማከናወን ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው ጥናቱ በቅርቡ ተጠናቆ የእድሳት ስራው ይጀመራል ብለዋል።

አውደ- ርዕዩ በዘርፉ አዲስ ቴክኖሎጂ የተዋወቀበት መሆኑን ጠቁመው ለሌሎች ስራዎችም መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ጎብኚዎች በአካል በመገኘት የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን እንዲጎበኙ መነሳሳት እንደሚፈጥር ታምኖበታል።

May be an image of 2 people

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሾ፤ ኢትዮጵያን ሳቢ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የፈረንሳይ መንግስት ያልተቋረጠ እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ፈረንሳይ በቱሪዝም ላይ ብዙ ልምድ አላት በመሆኗ ልምዷንም ለማጋራት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

የፈረንሳይ የልማት ድርጅት ዳይሬክተር ሚስ ታይ ቫሌሬ በበኩላቸው ድርጅቱ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን የማስተዋወቅና የመጠበቅ ፕሮጀክትን በገንዘብና በቴክኒክ እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል።

May be an image of 1 person

በይፋ ለጎብኚዎች ክፍት የሆነው አውደ -ርዕይን ጨምሮ የአቅም ግንባታዎች ላይ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን እየተወጣ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ ለዚህም 577 ሚሊዮን ብር መመደቡን አመልክተዋል።

"ይህን ዓለም አቀፍ ቅርስ የመጠበቅ ስራዎች ላይ መሳተፍ በመቻላችን ደስተኞች ነን" ብለዋል።

አውደ ርዕዩ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በላልይበላ ከተማና በውጭ አገራት ጭምር ለዕይታ ይበቃል ተብሏል።

በሥነ -ስርዓቱ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የኃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም