የአደጋ ስጋት ቅነሳ መርሐ ግብር በልማት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ መፍጠር እያስቻለ ነው- የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

246

መስከረም 27/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የአደጋ ስጋት ቅነሳ መርሐ ግብር ከእርዳታ ይልቅ በልማት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ መፍጠር እያስቻለ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ጉባኤ የፊታችን ማክሰኞ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በመጋፈጥ ለዜጎች ደህንነት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወረርሽኞች፣ ግጭትና ሌሎችም የዜጎችን መሰረታዊ ኑሮ እየፈተኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሶማሌ፣ ኦሮሚያ ደቡብና አፋር ክልሎች የተከሰተው ድርቅ የዜጎች የህልውና መሰረት ተናግቶ ቀያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የዜጎችን መፈናቀልና እንግልት ለማስቀረት ኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስትራቴጂ ነድፋ እንደ ችግሮቹ አይነትና መጠን የመፍትሔ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር፣ ሴፍትኔት፣ የስራ ዕቅድ ፈጠራና ሌሎች የልማት እንቅስቃሴዎች የአደጋ ስጋትን የሚቀንሱ እርምጃዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ድርቅ ባለባቸው አካባቢዎች በቂ ውሃ በማቅረብ አርብቶ አደሮች ከቀያቸው ሳይፈናቀሉ ችግሩን እንዲቋቋሙ ይደረጋል ብለዋል።

አርብቶ አደሩ ከመሰረታዊ ህይወቱ ሳይናጋ ባለበት እንዲቆይ መስኖ እንዲያለማ ማገዝና እንደ ጤና ተቋማት ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የውሀ ማቆሪያ /ቢርካ/ በማዘጋጀት በመስኖ ልማት በማሳተፍና አፈሩ በጎርፍ እንዳይሸረሸር ክትር በመስራት በ2014 በጀት ዓመት ብቻ ከ146 ሺህ በላይ ሰዎችን ከአደጋ ተጋላጭነት ስጋት እንዲወጡ ተደርጓል ብለዋል።

የአደጋ ተጋላጭነት ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው እርዳታ የሚጠብቁ ሳይሆን በራሳቸው መልማት የሚችሉበት አስተሳሰብ መፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል።

በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የሚከበረው ዓለም አቀፉ የአደጋ ስጋት ጉባኤ "የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መረጃ ለዘርፈ ብዙ ምላሽ" በሚል መሪ ሃሳብ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም