ቀጥታ፡

የብሔራዊ ፈተና አሰጣጥ ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁላችንም ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል -ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ

ዲላ መስከረም 27/2015 (ኢዜአ) የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና አሰጣጥ ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ በመምራት ሁላችንም ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ ተናገሩ ።

 ዶክተር ዲላሞ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የዲላ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት እንዳመለከቱት፤ ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ የተወሰነው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል፣ ትውልድን ከኩረጃና ማጭበርበር ለማላቀቅ ታስቦ ነው።

የተቀመጠውን ግብ በማሳካቱ ረገድ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ዝግጅት የሚመሰገን መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሲደረግ የቆየው ዝግጅትም ፈተናውን ከስጋትና ኩረጃ ነጻ በሆነ መንገድ ለመስጠት መሆኑን የገለጹት ዶክተር ዲላሞ፤ ባለድርሻ አካላት ቅንጅታችንን በማጠናከር የፈተና አሰጣጥ ሂደት ፍጹም ሰላማዊና የተረጋጋ በሆነ መንገድ በስኬት ማጠናቀቅ አለብን ብለዋል።

በተለይ ተማሪዎች በተረጋጋ መንፈስ ፈተናውን እንዲሰሩና የጥረታቸውን ውጤት እንዲያገኙ ሁሉም አካላት ምቹ  አካባቢ ለመፍጠር መትጋት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍቃዱ ወልደማርያም በበኩላቸው፤ ፈተናው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ከፌዴራል ፖሊስና ከአካባቢው የጸጥታ ግብረ ኃይል ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ዝግጅቱን አጠናቆ ከጌዴኦ ዞንና ከአጎራባች የሲዳማ ክልል ወረዳዎች ተፈታኝ ተማሪዎችን መቀበል መጀመሩን ገልጸዋል።

ተማሪዎች ከወረዳቸው ተነስተው ወደ ዩኒቨርሲቲው በመግባት ፈተና ወስደው ወደ ቤታቸው እስከሚመለሱ ድረስ አሰፈላጊው ትብብርና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ ናቸው።

በተለይ ለተማሪዎች የመጓጓዣ አገልግሎት በማመቻቸትና ደህንነታቸው ተጠብቆ መፈተኛ ማዕከላቸው የማድረሱ ተግባር በሃላፊነት እየተወጡ መሆኑን አስታውቀዋል።

በውይይቱም የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣  የፈተና ዝግጅት ግብረ ኃይል፣ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር አካላት፣ የፌዴራል ፖሊስ ተወካዮችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት መሳተፋቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም