በስምንት ከተሞች ሲከናወን የቆየው የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ መስመር ማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሥራ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በስምንት ከተሞች ሲከናወን የቆየው የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ መስመር ማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሥራ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ መስከረም 26/2015 (ኢዜአ) አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ በስምንት ከተሞች ሲከናወን የቆየው የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ መስመር ማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሥራ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ከሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ፤ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ተደራሽነቱን የማስፋት ስራ በስፋት በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን ለማስቀረትና የኔትወርክ ማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናረዋል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ በ50 ኪሎ ሜትር ራዲየስ የሚገኙ ከተሞች የዚሁ የልማት ክንውን አካል መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በወላይታ ሶዶ፣ ሐረር፣ ሻሸመኔ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ኮምቦልቻና ጎንደር ከተሞች ተመሳሳይ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ካጋጠመ ለአስቸኳይ ጥገና ወደ አንድ ማዕከል መረጃ የሚደርስበት ቴክኖሎጂ ተግባራዊ መደረጉንም ተናግረዋል።
የማሻሻያና የጥገና ሥራው በተለያዩ ምክንያቶች የኃይል መቋረጥ ካጋጠመ ከሌላ መስመር የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያገኝበት የአሰራር ስርአት ተዘርግቷል ብለዋል።
ከኤሌክትሪክ ማሰራጫና ማስተላለፊያ መስመር እርቀው የሚገኙ ከተሞች ከፀሐይ ኃይል እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መላኩ 25 ከተሞችንና የገጠር መንደሮችንም የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ የግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።