የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመስጠት በዩኒቨርሲቲዎች ያለው ዝግጅት አመርቂ ነው - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

254

አዳማ፣ መስከረም 26 ቀን 2015 (ኢዜአ) የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመስጠት በዩኒቨርሲቲዎች ያለው ዝግጅት አመርቂ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለፁ።

ሚኒስትሩ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ፈተናውን ለመስጠት ያለውን ዝግጅት ተመልክተዋል።

የፈተና መስጫ ቦታዎች፣ የመኝታ ክፍሎች ምቹነት፣ የፀጥታና ደህንነት ዝግጅት አመርቂ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲዎች ያለው ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ ፈተናውን ለመስጠትና ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

May be an image of 8 people and people standing

ዝግጅቱ ፈተናውን በጥሩ ሁኔታ መስጠት እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ ተማሪዎች ምንም አይነት ስጋት ሳይኖርባቸው ፈተናውን የሚወስዱበት ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው ገብተው ያሉ ተፈታኞች ፈተናውን ለመፈተን በሙሉ ሞራል ላይ መሆናቸውን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የምግብና የጤና አገልግሎት ዝግጅት በመልካም ሁኔታ መሰናዳቱን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ትምህርት ቤቶችና የየክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ የፀጥታ አካላትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አሁን ላለው ዝግጅት ሚናቸው የጎላ መሆኑን አስታውቀዋል።

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መስጠታችን እንደ ሀገር ያለንን አቅም የፈተሽንበትና ማድረግ እንደሚቻል ራሳችንን የለካንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

May be an image of 1 person and indoor

በዚህም ለፈተናዎች ደህንነት የተሻለ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው፤ ከእንግዲህ የፈተና ውጤት ማግኘትና ማለፍ የሚቻለው በትጋትና በታታሪነት ብቻ ነው ብለዋል።

ከፌዴራል ጀምሮ የክልሎችና የአካባቢው የፀጥታ አካላትና መስተዳድሮች እንዲሁም ዩኒቨርስቲዎች በፀጥታና ደህንነት ጉዳይ ላይ በጋራ እየሰሩ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ከመስከረም 30/2015 ጀምሮ ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እየገቡ ሲሆን ከ975 ሺህ በላይ ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም